ምስራቅ ኢትዮጵያ የሚታወቅበትን የፍቅርና የአብሮነት እሴት ለማጠናከር እንደሚሰራ ተገለፀ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 24 ፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬደዋ ከተማ አስተዳደርና የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፖርቲ መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ቀጥሎ እየተካሄደ ይገኛል።
እየተካሄደ በሚገኘው ስልጠና ላይም የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሞሃመድ ፣የሐረር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪና የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ በዚህ ወቅት÷ ብልጽግና ፖርቲ በምስራቅ ኢትዮጵያ ጥንት ጀምሮ የሚታወቀውን የፍቅር፣ የሃይማኖት መቻቻል፣ የመከባበር ባህልና የአብሮነት እሴቶችን ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል።
አቶ ሙስጠፌ ሞሃመድ በንግግራቸው ህዝቦች ያነሱትን የለውጥ ጥያቄ መነሻ በማድረግ ባለፉት ሁለት አመታት የህግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያ፣ ሰላምና ፍትህን ከማረጋገጥ አኳያ እንዲሁም ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አኳያ በተጀመሩ ስራዎች አበረታች ውጤቶች እየታዩ መሆኑን ገልፀዋል።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው ÷ የብልፅግና ፓርቲ የሚመራበት የመደመር ፍልስፍና የህዝቦችን እኩልነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልፀዋል።
አቶ ኦርዲን በድሪ አያይዘውም የህዝቦች ማንነትንና ሀገራዊ አንድነትን አዋህዶ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲሄድ የሚያደርግ በመሆኑ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
ሁለቱ ርዕሰ መስተዳድሮች ስልጠናውን እየወሰዱ የሚገኙ የድሬዳዋ አስተዳደርና የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፖርቲ መካከለኛ አመራሮች ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት በየአካባቢያቸው ተግባራዊ እንዲያደርጉና ከህዝብ የሚነሱ የመስረተ ልማት ጥያቄዎችን በአግባቡ እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረባቸው ተጠቁሟል።