የሐረሪ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት የክልሉ ህዝብ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመቀናጀት አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ ጥሪ አቀረበ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የኢድ አልፈጥር በዓልን በሀገር ቤት እንዲያከብሩ ያስተላለፉትን ጥሪ ተከትሎ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን በክልላችንም በዓሉ የተሳካ እንዲሆን ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
በተለይም በክልሉ በልዩ ሁኔታ የሚከበረው ሸዋል ኢድ እንዲሁም የኢድ አልፈጥር በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ የክልሉ የፀጥታ ሀይል ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከብሔራዊ መረጃ እና ደሕንነት፣ ከፌደራል ፖሊስና ከኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ሀይል እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየሰራ ይገኛል።
ለዚህ ስራ ውጤታማነትም ግብረሃይል ተቋቁሞ በየጊዜው በክልሉ የፀጥታው ምክር ቤት እየተገመገመ መልካም ተግባራት እንዲጎለብቱ እና በሂደቱ የታዩ ክፍተቶችም በአፋጣኝ እንዲታረሙ እየተደረገ ነው።
በመሆኑም በተለይም በትንሣኤ በዓል እለት በሸንኮር ወረዳ ዮድ ካፌና ሬስቶራንት ፀረ ሰላም ሀይሎች በወረወሩት ቦንብ ቦታው በነበሩ ዜጎች ላይ በደረሰው የአካል ጉዳት የክልሉ ፀጥታ ምክር ቤት ማዘኑን እየገለፀ ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር የማድረግ እና የምርመራ የማካሄድ ተግባር በሚመለከተው አካል እየተካሄደ ይገኛል።
ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን በአፋጣኝ ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ በቁርጠኝነት እንደሚፈጸም እየገለፀ መሰል ተግባራት በጭራሽ እንዳይደገም አጥብቆ የሚሰራ ይሆናል።
ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የብሄር እና የሀይማኖት ግጭት ለመፍጠር እና በክልሉ ሰላም እንደሌለ አድርገው በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ቅስቀሳ በሚያደርጉ እና የሀሰት መረጃ በሚያሰራጩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ምክር ቤቱ በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ ይወዳል።
የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና አስተማማኝ ሰላምን በማስፈን የሕዝብን ደኅንነት ማስከበር ቀዳሚ ተግባር በመሆኑ የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት በክልሉ ሰላም እንዲጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ገልጿል።
መጪዎቹ በዓላትም ካለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቁም በተለይ የፀጥታ ሀይልን በማጠናከር፣ በተመረጡ አካባቢዎች ተገቢውን ፍተሻና ቁጥጥር በማድረግ እንዲሁም ህዝብን በላቀ ደረጃ በማቀናጀት በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቋል።
በመሆኑም ሰላም ወዳዱ የክልላችን ህዝብ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመቀናጀት እና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ዛሬም እንደ ትናንቱ የክልላችን ህዝቦች በሰላም፣ በአብሮነት እና በመቻቻል የሚኖሩባት ክልል መሆኗን በተግባር እንደሚያረጋግጥ ያለውን እምነት ገልጿል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!