ቻይና 4ኛውን ምዕራፍ ጨረቃን የማሰስ መርሃ ግብር በዚህ ዓመት እንደምትጀምር አስታወቀች
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና አራተኛውን ምዕራፍ ጨረቃን የማሰስ መርሃ-ግብር በዚህ ዓመት ልትጀምር መሆኑን የቻይና ብሔራዊ የጠፈር አስተዳደር ምክትል ኃላፊ ው ያንሁዋ ተናገሩ።
የአራተኛው ምዕራፍ ጨረቃን የማሰስ መርሃ-ግብር ዓላማም በደቡባዊ የጨረቃ ዋልታ ላይ ሣይንሳዊ ቅኝት ለማካሄድ እና በቀጣይ በአካባቢው ለመገንባት የታሰበውን የጥናት ጣቢያ መሠረታዊ ንድፍ ለማሳለጥ ነው ተብሏል፡፡
በጨረቃ ደቡባዊ ዋልታ ላይ የሚሰራው የጥናት እና የምርምር ማዕከል ለሁሉም ሀገራት ክፍት እንደሚሆንና ሀገራቱ እና በዘርፉ ላይ የሚሰሩ የተለያዩ ድርጅቶች በየተራ የሚመሩት ማዕከል እንደሚሆንም ነው የተናገሩት፡፡
በጨረቃ ላይ የሚከናወነው ሂደት ሦስት ደረጃዎች እንደሚኖሩትና ሂደቶቹም ግልጽነት እና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን እንዲያጎለብቱ ታሳቢ የተደረጉ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት የጨረቃን ከባቢ የመቃኘት እና መሠረታዊ ግንባታዎችን የማከናወን ሥራ የሚከናወን ሲሆን፥ በሁለተኛው አሥር ዓመት ደግሞ ሁሉን አቀፍ የሆነ ተወዳዳሪ የሣይንስ ጣቢያ ይገነባል ነው ያሉት።
በሥራው ላይ የተለያዩ ሀገራት እና ድርጅቶች (የግሉን ዘርፍ ጨምሮ) ተሳትፎ እንደሚኖርም ነው የተመለከተው፡፡
ሦስተኛው ደረጃም ወደ ተግባር መግባትና ሣይንሳዊ ግኝቶችን ለዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ማበርከት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ቻይና ዓለም አቀፋዊ ማኅበረሰብን ለመፍጠርና የሁሉንም ሀገራት የወደፊት ተሥፋ የሚያለመልም የጠፈር ምርምር ለማካሄድ እንደምትፈልግ የቻይና ብሔራዊ የጠፈር አስተዳደር ማስታወቁን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡
ቻይና በመጀመሪያው ምዕራፍ መርሃ -ግብሯ በፈረንጆቹ 2007 ላይ የጨረቃን ምህዋር የሚዞር ሮኬት በማስወንጨፍ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን እና ጨረቃን በጥልቀት መመልከት የሚያስችሉ ፎቶዎችን ወስዳለች።
በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ መንኩራኩሯን በፈረንጆቹ 2013 ጨረቃ ላይ በተሳካ ሁኔታ ስታሳርፍ፥ በሦስተኛው ምዕራፍም በተመሳሳይ መንኩራኩር በፈረንጆቹ 2014 ልካ 2 ኪሎ ግራም የጨረቃ አፈር ናሙና ይዛ ወደ ምድር እንደተመለሰች በቻይና ሉናር ኤክስፕሎሬሽን ፕሮግራም መረጃ ተመላክቷል፡፡https://www.youtube.com/watch?v=8GdUOVbIMbo