ሚኒስቴሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ3 ሺህ 700 በላይ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአገር አቀፍ ደረጃ ከ3 ሺህ 700 በላይ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በመጠጥ ውሃ ማስተባበሪያ ፕሮግራም እየተገነቡ መሆኑን የውሃ እና ኢነርጅ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የውሃ እና ኢነርጅ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ለፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷በገጠር እና ከተማ እየተገነቡ የሚገኙት የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች አብዛኞቹ በተያዘው በጀት ዓመት የሚጠናቀቁ ናቸው።
በጀት ዓመቱ እስኪጠናቀቅ ድረስም ከ 4 ሚሊየን በላይ ተጨማሪ ሰዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በየአካባቢው የሚነሱ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት ችግሮችን ለመፍታትም በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው÷ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ አንስተዋል።
በዋን ዎሽ በመጠጥ ውሃ ማስተባበሪያ ፕሮግራም ከ 3ሺህ 700 በላይ የመጠጥ ውሃፕሮጄክቶች እየተገነቡ ሲሆን ÷3ሺህ 724 የሚሆኑት በገጠር 60ዎቹ ደግሞ በከተማ እንደሚገነቡ ተጠቁሟል፡፡
በዋን ዎሽ ፕሮግራም እየተገነቡ የሚገኙት ከ 3ሺህ 700 በላይ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በሙሉ እስከሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ግንባታቸው የሚጠናቀቅ መሆኑን አምባሳደር አስፋው ተናግረዋል።
በዚህ ፕሮግራም ከሚገነቡት በተጨማሪ በድርቅ የተጎዱ ውሃ አጠር የሆኑ አካባቢዎች ላይም 63 ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆናቸውን አንስተዋል።
በጸሃይ ኃይል የሚሰሩ የውሃ አቅርቦቶች፣ የፍሎራይድ መከላከል ፕሮጄክት በሚባሉት አማራጮችም ፕሮጀክቶቹን በመገንባት የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሰራ ነውም ብለዋል።
አዳዲስ የመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶችን ከማስፋፋት በተጨማሪም በተለይም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ላይ የጥናት ቡድን በማሰማራትም ጥናት የተከናወነ ሲሆን÷የደረሰውን ጉዳት መነሻ በማድረግም ስራዎች ይሰራሉ ተብሏል።
በዙፋን ካሳሁን