ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ጋር በትብብር እና ድጋፍ መስኮች ላይ ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መዓዛ አሸናፊ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን ጋር በዋና ዋና የትብብር እና የድጋፍ መስኮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን በዛሬው ዕለት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የጎበኙ ሲሆን፥ በቆይታቸውም በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤሰ አይድ) በኩል ለፍርድ ቤቱ ስለሚደረጉ ዋና ዋና የትብብር እና የድጋፍ መስኮች እንደተወያዩ ከማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በዩኤሰ አይድ በኩል የሚደረገው ድጋፍ በተለይም የፍትህ ሥርዓቱን ለማሻሻል እና ላለፉት ሁለት ዓመታት ፍርድ ቤቱ ሲያከናውናቸው የቆዩ የሪፎርም መርሀ-ግብሮችን ለመደገፍና ለማጠናከር እንደሚውል ተገልጿል።
በተጨማሪም የፍትህ አካላት ሚና ፣ የፍርድ ሥርዓቱ ግልፅነትና ተጠያቂነት ላይ እንዲሁም ሁለቱ አካላት ስለሚኖራቸው ቀጣይ ግንኙነት መወያየታቸውም ተመላክቷል፡፡