በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስተባባሪነት በተካሄደው የጀነሬሽን አንሊሚትድ ችግር ፈቺ የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር አሸናፊ ቡድኖች ተለዩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስተባባሪነት ሲካሄድ በቆየው የጀነሬሽን አንሊሚትድ የወጣቶች ችግር ፈቺ የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር አሸናፊ የሆኑ ሁለት ቡድኖች መለየታቸውን ሚኒስቴሩ አስታወቀ፡፡
በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተዘጋጀው የጀነሬሽን አንሊሚትድ የወጣቶች ችግር ፈቺ የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር÷ ኮፊ ሌዘንስ እና ሼባ በብልስ ቡድኖች አሸናፊ ሆነዋል፡፡
ኮፊ ሌዘንስ በአራት ወንዶች የተመሰረተ እና የፕሮግራም ኮዲንግ ላይ የሠራ የወጣቶች ቡድን ሲሆን÷ ሼባ በብልስ በሦስት ሴት ወጣቶች የተመሰረተ እና ለመተንፈስ የሚረዳ ማሽን የሰሩ ወጣቶች ቡድን ነው፡፡
ለዓለም አቀፉ ውድድር የተመረጡት ሁለቱ አሸናፊ ቡድኖች በመጪው ነሐሴ ወር ኒውዮርክ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ከ35 አገራት ከተውጣጡ ሥራ ፈጣሪ ሃሳቦች ጋር ውድድራቸውን ያካሂዳሉ፡፡
በዓለም አቀፉ ይሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዘላቂ የልማት ግቦችን መሠረት አድርጎ ሲካሄድ በቆየው ውድድር አሸናፊ የሆኑት አምስቱም ቡድኖች በማስተርካርድ ፋውንዴሽን የተዘጋጀውን 230 ሺህ ብር ተሸልመዋል፡፡ ከአምስቱ ውጪ ተመርጠው የነበሩት አምስት ቡድኖችም 130 ሺህ ብር ተሸልመዋል፡፡
ሽልማቱን ያበረከቱት በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን እንደገለጹት÷ በአገራችን ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስቸጋሪ የሆኑት የክህሎት እጥረት፣ የድጋፍ ማጣት እና የትስስር ችግሮች ናቸው፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመቀነስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወጣቶች የንግድ ሥራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድሮች እንደሚያዘጋጅ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ይህ የጀነሬሽን አንሊሚትድ የወጣቶች ውድድር ደግሞ የማህበረሰቡን ችግሮች የሚፈታ ሃሳብን እና የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ የሚያበረታታ እና በዓለም ላይ በሃሳብ መወዳደር የሚያስችል ፈር ቀዳጅ ሥራ በመሆኑ ለዚህ የተባበሩትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!