የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ያለማቸውን አራት ቴክኖሎጂዎች ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ያለማቸውን 3ዲ ፕሪንተር፣ ፕላንት ዌት (መሬት ላይ ሆኖ በየትኛውም የህዋ አካል ላይ ክብደትን ለማወቅ የሚያስችል ቴክኖሎጂ) ባለ 70 ሚሊሜትር ሪፍራክተር ቴሌስኮፕ እና ባለ 200 ሚሊ ሜትር ቴሌስኮፕ አራት ቴክኖሎጂዎች ይፋ አደረገ፡፡
የኢንስቲቱዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ፤ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ባለስልጣን ኢንስቲትዩቱ ላለማቸው ቴክኖሎጂዎች የባለቤትነት እውቅና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳሮች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲዎችና ተቋማት ባለሙያዎች ቴክኖሎጂዎችን ለማበልጸግ የሚያስችላቸውን ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉንም እንዲሁ፡፡
ስልጠናውን ከወሰዱት መካከል ከሲዳማ ክልል የመጡት ወይዘሮ ቤተልሔም ዳንኤል በስልጠናው ያገኙትን እውቀት በክልሉ ለሚገኙ ተማሪዎች በማካፈል ተግባራዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡
ከድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር የመጡት አቶ ኢማም አብዱልቃድር በበኩላቸው ያገኙትን ስልጠናና ልምድ በክልላቸው ለሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እንደሚያካፍሉ ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
እንደ ሀገር ትልቅ ደረጃ ለመድረስ የያዝነው ውጥን የሚሳካው ወጣቶችን በቴክኖሎጂ ማነጽ ስንችል ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም በኢንስቲትዩቱ የበለጸጉትን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በስፋት በማቅረብ ወጣቶችን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡