ትምህርት ከሀይማኖታዊ እንቅስቃሴ ነጻ በሆነ ሁኔታ መካሄድ አለበት – የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ትምህርት ከማንኛውም ሀይማኖታዊ እንቅስቃሴ ነጻ በሆነ ሁኔታ መካሄድ እንዳለበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አሳሰበ፡፡
ቢሮው በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ከሀይማኖት ጋር በተያያዘ በተስተዋሉ ጉዳዮች ላይ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሠ መምህራን ጋር ተወያይቷል፡፡
በውይይቱም በየትምህርት ቤቱ ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ እና የተማሪዎች መተዳደሪያ ደንብን በሚጻረር መልኩ የሚስተዋሉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ተነስቷል፡፡
በዚህም አንዳንድ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ሀይማኖትን መሰረት ባደረጉ እንቅስቃሴዎች ለመሳተፍ ሙከራ የማድረግ አዝማሚያ ማሳየታቸው÷ ከውጭ ሆነው ተማሪዎቹን ወደ አላስፈላጊ ሁኔታዎች የሚገፋፉ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው አካላት መኖራቸው ተመላክቷል፡፡
በመሆኑም ትምህርት ከሀይማኖታዊ እንቅስቃሴ ነጻ በመሆነ ሁኔታ የሚከወን ቢሆንም÷ ይህን አለም አቀፍ ህግ በሚጻረር መልኩ በአንዳንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚስተዋሉ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ትምህርት ቤቶች ወጥ በሆነ መልኩ ተማሪዎች በማንኛውም የትምህርት ሰዓት ከግቢ እንዳይወጡ በማድረግ በኩል ርዕሠ መምህራን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በመጭው ቅዳሜና እሁድ ትምህርት ቤቶች ከተማሪ ወላጆች ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት ይደረጋል መባሉን ከከተማ አስዳድሩ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!