Fana: At a Speed of Life!

የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ግንባታ የሲቪል ስራ ከ90 በመቶ በላይ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ግንባታ ፕሮጀክት የሲቪል ስራ ከ90 በመቶው በላይ መጠናቀቁን የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አስታወቀ።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለና ካቢኔያቸው ዛሬ የፕሮጀክቱን የስራ እንቅስቃሴ በስፍራው በመገኘት ተመልክተዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ፍሰሃ አሰፋ በወቅቱ ግንባታው ከመደበኛው የስራ ሰዓት ውጭ ምሽትም ጭምር እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በአሁኑ ወቅት የግንባታ ስራው የመሬት አቀማማጥ ማስተካከል ስራን ጨምሮ ወደ ማጠናቀቂያ የምዕራፍ ተግባራት መሸጋገሩን ተናግረዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ግንባታ አለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የጣናን ውበት በሚያጎላና ከአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ጋር በሚስማማ መልኩ በድንቅ የቱሪዝም የጥበብ ስራዎች የተቃኘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የግንባታ ስራው በሺዎች ለሚቆጠሩ የአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠሩም በላይ ለእውቀትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ግንባታ ሲጠናቀቅ ሰፋፊ የስብሰባ አዳራሾች፣ ዘመናዊ የእንግዳ ማረፊያዎች፣ መዝናኛ ሎጆችና የአምፊ ቲያትር ማሳያ ሥፍራዎች ማካተቱን አስረድተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የባህር ላይ መዝናኛዎች ፣የእግረኞችና የብስክሌተኞች መጓጓዣ መንገዶችና ሁለት የሄሊኮፕተር ማረፊዎችን ያካተተ ሲሆን÷ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ቱሪስቶች ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ ነው ሲሉ ዶክተር ፍሰሃ በቦታው ለተገኙት ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች አብራርተዋል፡፡

 

በሌላ በኩል ርዕሰ መስተዳድሩ የአንገረብ የመጠጥ ውሃ ግድብን የሥራ አፈጻጸም ዛሬ ማምሻውን ተመልክተዋል፡፡

የጎንደር ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በማገዝ በኩል የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ነው ዶክተር ይልቃል የተናገሩት፡፡

በከተማው በፍጥነት እየጨመረ ከመጣው  የነዋሪው ህዝብ ቁጥር አንጻር የንጹህ መጠጥ ውሃ  አቅርቦት በበቂ መጠን ማዳረስ አልተቻለም ብለዋል፡፡

የከተማውን  የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ከመፍታት አንጻር የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ግንባታ እንዲፋጠን ጥረት እንደሚደረግ ገልጸው፤  ሌሎች አማራጮችን ማመቻቸት ጊዜ የሚሰጠው ተግባር አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለረጅም ዓመታት አገልግሎት የሰጠውን የአንገረብ የመጠጥ ውሃ ግድብ በደለል  የመሞላት ችግር በመፍታት  በቴክኖሎጂ  ታግዞ  ውሃ የመያዝ አቅሙን ለማሳደግ የተጀመረውን ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.