ከሳዑዲ ዓረቢያ ተመላሾችን ከአቀባበል እስከ መልሶ ማቋቋም ያለውን ሂደት ለማሳለጥ በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሳዑዲ ዓረቢያ ስደት ተመላሾችን ከአቀባበል ጀምሮ እስከ መልሶ ማቋቋም ያለውን ሂደት ውጤታማ ለማድረግ ዝግጅት ተጠናቆ ወደስራ መግባቱን የስደተኞች አቀባበል ብሔራዊ ኮሚቴ አስታወቀ።
በሳዑዲ እስር ቤቶች በችግር ውስጥ የነበሩ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን የመመለስና መልሶ የማቋቋም ሂደቱን ለማሳለጥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተለያዩ ባለድርሻ ተቋማት የተካተቱበት ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንደገለጹት÷ የተለያዩ የዲፕሎማሲ ተግባራትን በማከናወን ዜጎችን ወደ አገር የመመለሱ ሂደት ተጀምሯል፡፡
በዚህም በ11 ወራት ውስጥ ከ102 ሺህ በላይ ዜጎች ወደአገር ቤት ለመመለስ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን÷ ዛሬ በመጀመሪያ ዙር በረራ ወደ 500 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ከ40 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ መመዝገባቸውን ገልጸው÷ ስደተኞችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን እና በአዲስ አበባም ጊዜያዊ ማረፊያ መዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡
አስፈላጊውን ስልጠና እናተሃድሶ በመስጠት ተመላሾቹን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
የኮሚቴው አባልና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው÷ ተመላሾቹን ለማቋቋም ዝግጅት መደረጉን ገልጸው÷ በተለይም ለአረጋውያን፣ ሴቶችና ህጻናት ቅድሚያ ይሰጣል ብለዋል።
የስደተኞችና ስደት ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው÷ ተመላሾቹ ለችግር እንዳይጋለጡ ከ16 ባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
በዚህም ተመላሾችን ከማህበረሰቡ ለመቀላቀልና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደሚደረጉም ገልጸዋል።
በመዲናዋ ለስደት ተመላሾች በተዘጋጁ ጊዜያዊ ማረፊያዎች የምግብ፣ አልባሳት፣ መገልገያ ቁሳቁስ መዘጋጀቱን የገለጹት ደግሞ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክትል ኮሚሽነር አቶ ነሲቡ ያሲን ናቸው።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሰሃርላ አብዱላሂ÷ ጤና ሚኒስቴር ከስደት ለተመለሱ ዜጎች የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮና ሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።
ስደተኞች በብዛት የጤና እክል ስለሚያጋጥማቸው ከሆስፒታሎች ባሻገር ተኝተው ለሚታከሙ በተጠባባቂነት “ቦሌ ጨፋ” በሚባል ስፍራ የህክምና ማዕከል መዘጋጀቱን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!