Fana: At a Speed of Life!

ከነበርንበት አስከፊ ሁኔታ ወጥተን ለሀገራችን በመብቃታችን ተደስተናል- የሳዑዲ ተመላሾች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳዑዲ ዓረቢያ እስር ቤቶች ከነበሩበት አስከፊ ሁኔታ ወጥተው ለሀገራቸው በመብቃታቸው መደሰታቸውን ከሳዑዲ የተመለሱ ዜጎች ተናገሩ፡፡
ዛሬ በሪያድ ከተማ ከሚገኙ እስር ቤቶች ወጥተው አዲስ አበባ የደረሱ ዜጎች የደስታ ስሜታቸውን በተለያየ መልኩ ገልጸዋል፡፡
መንግስት በእስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገር ቤት ለመመለስ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡
በሳዑዲ ዓረቢያ ከ750 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን÷ ከእነዚህ ውስጥም ከ450 ሺህ በላይ የሚሆኑት በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ የገቡ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ዓረቢያ ለእስር የተዳረጉ ሲሆን÷ መንግስት በእስር ቤት የሚገኙ ዜጎችን ለመመለስ የተለያዩ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን ሲያከናውን ቆይቶ ዛሬ ወደ አገር ቤት የመመለሱ ስራ በይፋ ተጀምሯል፡፡
በእስር ቤት የቆዩ አስተያየት ሰጭዎች እንደገለጹት÷ ከበርካታ የችግር ጊዜያት በኋላ ወደ እናት አገራቸው በመመለሳቸው እጅግ መደሰታቸውን ገልጸው÷ መንግስት ሌሎች በእስር ቤቱ የሚንገላቱ ወገኖችን በተቻለው አቅም እንዲመልሳቸውም ጠይቀዋል።
ህገ-ወጥ ስደት በእኛ ይብቃ ሲሉም ለሌሎች ኢትዮጵያውያን መልዕክት አስተላለፈዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ገንበቶ በበኩላቸው ÷ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ወደ አገር ቤት የሚመለሱ ዜጎችን ሁኔታ የማረጋገጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ስደተኞችን የመመለስ ስራ ውስብስብ ሂደት እንዳለው ጠቅሰው÷ የሳዑዲ ዓረቢያና በኢትዮጵያ መንግስት መግባባት ተደርሶ በሳምንት 9 በረራዎችን በማድረግ ዜጎችን የመመለስ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.