Fana: At a Speed of Life!

ድርጅቱ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በባህር ትራንስፖርትና የገቢ እቃዎች ላይ ለተፈጠረው ጫና አማራጮች እየተፈለጉ ነው አለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና የገቢ እቃዎች ማጓጓዝ ላይ ለፈጠረው ጫና አማራጮች እየተፈለጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ።

ጦርነቱ ከተጀመረ አንድ ወር ባለፈው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫናዎችን ማሳደሩ ተመላክቷል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካሳደረው ጫና በማገገም ላይ የነበረው የዓለም የንግድ መዛባት አሁን ላይ በሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ሌላ ጫና ተፈጥሮበታል።

በተለይ የምግብ፣ የነዳጅ፣ የዘይትና ሌሎች ምርቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው ሲሆኑ÷ጦርነቱ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ላይም ጉዳት እያስከተለ ነው ተብሏል።

የሁለቱ አገሮች ጦርነት ለዘርፉ ከባድ ፈተና ደቅኗል ያሉት የባህር ትራንስፖርት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ወንድወሰን ካሳ÷ የኢትዮጵያ መርከቦች የአገልግሎት ወጪ እየጨመረ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይም የነዳጅ ወጪያቸው ካለፉት 6 ወራት ወዲህ የ42 በመቶ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ጠቅሰው÷ የጦርነቱ ተፋላሚ አገራት የአውሮፓና የኤዥያ መተላለፊያ በመሆናቸው በባቡር ለሚጓጓዙ ምርቶች ከፍተኛ ችግር ሆኗል ብለዋል።

በ2021 እስከ 1 ነጥብ 5 ኮንቴይነሮች በባቡር መጓጓዛቸውን ገልጸው÷ በዚህ ዓመት የሚቋረጥ ከሆነ ከ5 እስከ 8 በመቶ እቃዎች ወደ ባህር ትራንስፖርት ሊመጡና ጫና ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ጦርነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የባህር ትራንስፖርት እጥረትና በባህር በሚጓጓዙ እቃዎች ላይ የጭነት የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል ይችላል ነው ያሉት።

የሁለቱ አገሮች ጦርነት እልባት ካላገኘ በባህር ትራንስፖርቱ ላይ የሚፈጠረው ጫና ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችልም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የባህር ትራንስፖርቱ አሁን ካለበት ጫና ይበልጥ ወደ ከፋ ችግር እንዳይሸጋገር ለሚገቡ ምርቶች አማራጭ መንገዶችን መፈለግ ይገባልም ብለዋል አቶ ወንድወሰን።

ከጥቁር ባህር አካባቢ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ አማራጮች በሌሎች አገራት መኖራቸውን የተናገሩት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ከኦማን የብረት ምርት በማስገባት ላይ እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።

ከህንድ ብረትና የስንዴ ምርት የማስገባት አማራጭ መኖሩን ጠቅሰው÷ ካናዳና አርጀንቲናም የስንዴ አምራች አገራት በመሆናቸው የተለያዩ አማራጮችን ማየት ይጠቅማል ነው ያሉት።

የሱፍ ዘይት በጦርነቱ ምክንያት ምርቱ ወደ ገበያ ባይቀርብም ከኢንዶኔዥያና ማሌዥያም የፓልም ዘይትንና በተወሰነ ደረጃም የሱፍ ዘይትን ማስገባት ይቻላል ብለዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.