ወንድሜ ኢስማኤል ዑመር ጌሌ ወደ ሁለተኛ ቤትዎ እንኳን በደህና መጡ -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ፣መጋቢት 18፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጅቡቲ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ወንድሜ ኢስማኤል ዑመር ጌሌ ጋር በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ ፍሬያማ ውይይት እንደምናደርግ እምነቴ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
የጅቡቲ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ዑመር ጌሌ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ ከሰዓት በኋላ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ÷ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ዑመር ጌሌ ዛሬ አዲስ አበባ መግባታቸውን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ወንድሜ ኢስማኤል ኦመር ጌሌ ወደ ሁለተኛ ቤትዎ እንኳን በደህና መጡ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም÷ “በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ ፍሬያማ ውይይት እንደምናደርግ እምነቴ ነው ብለዋል።
የፕሬዚዳንት ኢስማኤል ዑመር ጌሌ ጉብኝት ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን÷ የሁለቱ አገራት መሪዎችም በሁለትዮሽ አገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያና ጅቡቲ ለረዥም ዘመናት በባህልና በታሪክ የተሳሰሩ፥ የቆየና የጠበቀ የወዳጅነት ግንኙነት ያላቸው እህትማማች አገሮች ናቸው።
አገራቱ በባቡር፣ በመንገድ፣ በውሃ፣ በቴሌኮም፣ በኤሌክትሪክ ኃይል እና በሌሎችም የልማት መስኮች የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየሰሩ እንደሚገኙም ይታወቃል።
በአልአዛር ታደለ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!