Fana: At a Speed of Life!

አሉላ ገብረአምላክ የምዕራፍ ዘጠኝ የ”ፋና ላምሮት” ውድድር አሸናፊ ሆነ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምዕራፍ ዘጠኝ የ”ፋና ላምሮት” የባለተሰጥዖ ድምፃውያን ውድድር በዛሬው እለት ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡

ላለፉት ስምንት ሣምንታት ሲካሄድ የቆየው የ“ፋና ላምሮት” የምዕራፍ ዘጠኝ ውድድር ፣ ተወዳዳሪዎች ራሳቸው በመረጧቸው እና ዳኞች በመረጡላቸው ሙዚቃዎች ሲፈተኑ መቆየታቸው ይታወቃል።

“ፋና ላምሮት” በቀጥታ ስርጭት ሲካሄድ ከዳኞች ሙያዊ ዳኝነት በተጨማሪ ተመልካቾችም በ”8222” ላይ የተወዳዳሪዎችን ኮድ በመላክ ሲደግፉ መቆየታቸው ይታወሳል።

በዛሬው የባለተሰጥዖ ድምፃውያን ውድድር ላይም አድማጭ ተመልካቾች እንደቀደመው ሁሉ ያልተገደበ የ”ኤስ ኤም ኤስ መልዕክቶቻቸውን” በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ኮድ በመላክ ይገባዋል ለሚሉት ተወዳዳሪ ድምፃቸውን ሰጥተዋል፡፡

በዚህም በውድድሩ ላሸነፉ ድምፃውያንም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በምዕራፍ ዘጠኝ የ”ፋና ላምሮት” የባለተሰጥዖ ድምፃውያን ውድድር አንደኛ በመውጣት አሉላ ገብረአምላክ የ200 ሺህ ብር ፣ መክብብ አራጌ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ 150 ሺህ ብር ፣ ዘላለም ታደሰ ሶስተኛ በመውጣት 100 ሺህ ብር እንዲሁም ረቂቅ አሰግድ አራተኛ ደረጃ የ50 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ አቤል አዳሙ በውድድሩ ፍጻሜ ወቅት ተገኝተው እንደተናገሩት÷ ፋና ላምሮት የባለ ተሰጥዖ ድምፃውያን ውድድር በኢትዮጵያ ታሪክ የቀጥታ ስርጭት ያለው የድምጻውያን ውድድር መሆኑን አስታውሰው ፥ ውድድሩ መካሄድ ከጀመረ ጀምሮ በርካታ ባለ ተሰጥዖ ድምጻውያንን ማፍራቱን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ጥበብ እና ጥበበኞች ያሉባት ሀገር ናት ያሉት ምክትል ስራ አስፈጻሚው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በ”ፋና ላምሮት” የቀጥታ ስርጭት የባለተሰጥዖ ድምጻዊያን ውድድር በኩል እድሉን ያላገኙ ድምጻዊያን ተሳትፎ እንዲያደርጉ እድል በመፍጠር ጥበበኞችን ከጓዳ ወደ አደባባይ በማውጣት እየሰራ እንደሆነ እና በቀጣይም በየበታቸው የተደበቁ ኮከቦችን ወደ አደባባይ ማውጣቱን ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

ፕሮግራሙን ስፖንሰር ላደረጉ አጋር ድርጅቶች እና ተመልካቾች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.