ኢትዮጵያ ከውጪ የሚገባውን የስንዴ ምርት ለመተካት ክልሎች ጥረቶቻቸውን በማሳደግ ላይ ይገኛሉ- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመራ ልዑክ በምስራቅ ሸዋ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ጎበኘ።
በጉብኝቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የዓለም ባንክ ቦርድ ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ታዎፊላ ኒያማድዛቦ እናበኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን ተገኝተዋል፡፡
በተጨማሪም የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና ሌሎችም የፌዴራል እና የክልል የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
ጉብኝታቸውን አስመልክተውም÷ “በኦሮሚያ ክልል ተገኝተን ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ምርትን የመተካት ፍላጎታችን ማሳያ የሆኑትን የስንዴ ማሳዎች ጎብኝተናል” ብለዋል፡፡
አያይዘውም “ኢትዮጵያ ከውጪ የሚገባውን የስንዴ ምርት የሀገር ውስጥ ምርታማነትን በማሻሻል ለመተካት ባላት ፍላጎት መሠረት የሀገራችን ክልሎች ጥረቶቻቸውን በማሳደግ ላይ ይገኛሉ” ነው ያሉት፡፡
በብሄራዊ ደረጃ 400 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለማልማት የታቀደ ሲሆን÷ የኦሮሚያ ክልል ብቻውን 355 ሺህ130 ሄክታር ማሳካት መቻሉ በጉብኝቱ ተገልጿል፡፡
ባሳለፍነው እሁድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራ የሚኒስትሮችና የክልል ርዕሰ መስተዳደሮች ልዑካን ቡድን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ዋዋ ቀበሌ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መጎብኘቱ ይታወሳል፡፡
በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባደረጉት ንግግር፥ “ግብርና የሀገራችን የኢኮኖሚ መሠረት ሆኖ ቆይቷል፤ የስንዴ አቅርቦት በዓለም አቀፍ ሁነቶች ጫና እየደረሰበት በመሆኑ በምግብ ራሳችንን ለመቻል ምርታማነታችንን ማፋጠን በእጅጉ ያስፈልገናል” ብለዋል።
እየታየ ያለው ምርታማነት ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ “የግብርና ጉዟችን አድካሚ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ተጋድሏችን የምርታማነታችንን መጠን በሚሊዮኖች ለማስፋፋት ነው” ብለዋል፡፡
አመራሮች ከፓለቲካና ስብሰባ ጊዜ ቀንሰው ለኢኮኖሚው መስራት እንዳለባቸውም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳሰቡት፡፡
በአፈወርቅ አለሙ እና ዳግማዊ ዴክሲሳ