በኢ-ሜይል መልእክቶች ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች በ50 በመቶ መጨመሩ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በፈረንጆቹ 2021 ብቻ መሰረታቸውን ክላዉድ (cloud) ላይ ያደረጉ የኢ-ሜይል መልእክቶች ላይ ያነጣጠሩ የጥቃት ሙከራዎች 50 በመቶ ጭማሪ ማሳየታቸውን የትሬንድ ማይክሮ ሪፓርት ይፋ አድርጓል።
የሳይበር ደህንነት ምርት አቅራቢው “ትሬንድ ማይክሮ” በደንበኞቹ በተጫኑ ምርቶች እና ክላውድ ላይ መሰረቱን ባደረገ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት ዙሪያ መረጃዎችን በመሰብሰብ ባወጣው የ2021 ማጠቃለያ ሪፖርት÷ በኢ-ሜይል መልእክቶች ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መጨመራቸውን አመላክቷል።
በፈረንጆቹ 2021 ብቻ ከ4 ነጥብ 1 ቢሊየን በላይ የኢ-ሜይል ተጠቃሚዎች እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን÷ በአንድ ቀን ውስጥ የሚከናወኑ የኢ-ሜይል መልእክት ልውውጦች ላለፉት ዓመታት በቋሚነት ጨምረዋል፡፡ በ2020 ብቻ ከ333 ቢሊየን በላይመድረሱም ተመላክቷል፡፡
እንደ ትሬንድ ማይክሮ ሪፖርት÷ ኩባንያው በፈረንጆቹ 2021 ብቻ በጎግል ዎርክስፔስ እና ማይክሮሶፍት 365 ተጠቃሚዎች ላይ ያነጣጠሩ 25 ነጥብ 7 ሚሊየን የኢ-ሜይል ጥቃት ሙከራዎች ማገዱን ገልጿል፡፡ ይህ ቁጥር በፈረንጆቹ 2020 ከነበረው 16 ነጥብ 7 ሚሊየን አንጻር ከፍተኛ ልዩነት ማሳየቱም ነው የተመላከተው፡፡
ከአጠቃላይ የኢ-ሜይል ጥቃት ሙከራዎች ውስጥ መረጃ ማጥመድ (phishing) ሙከራዎች በእጥፍ መጨመራቸውን ኩባንያው ገልጿል፡፡
ከነዚህ ውስጥም በቤታቸዉ ሆነዉ ስራዎችን እየሰሩ ያሉ ግለሰቦች ለሳይበር ወንጀለኞች ኢላማ መሆናቸውን ገልጾ÷ 38 ከመቶ የሚሆኑ የኢ-ሜይል ጥቃት ሙከራዎች ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለመመንተፍ የታለሙ መሆናቸውን ኩባንያዉ ጠቁሟል።
ለእነዚህ ጥቃቶች መጨመር እንደዋና ምክንያትነት ከተቀመጡ ጉዳዮች መካከል በክላውድ ስርአት ውስጥ በተሳሳተ መንገድ የተዋቀሩ ስርዓቶች መፈጠር ሲሆን÷ በፈረንጆቹ 2021 ወሳኝ የጥቃት ተጋላጭነቶች ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን ትሬንድ ማክሮ በሪፓርቱ ማስታወቁን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያላክታል፡፡