Fana: At a Speed of Life!

በበጋ መስኖ እየለማ የሚገኘው የስንዴ ሰብል ተስፋ ሠጭ መሆኑን የአማራ ክልል ም/ቤት አባላት ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጎንደር ዙሪያ፣ በእንፍራንዝና ምዕራብ ደምቢያ ወረዳዎች በበጋ መስኖ የለማ የስንዴ ሰብልን ጎብኝተዋል።
 
በጉብኝቱ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር  ጀነራል ተመሥገን ጥሩነህን ጨምሮ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ዶ/ር ጌታቸው ጀምበር ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
 
በጉብኝቱ ላይ አሚኮ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ሰብላቸው ጥሩ ምርት ሊያስገኝ በሚችል ቁመና ላይ መኾኑን ተናግረዋል።
 
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኀላፊ ዶ/ር ኃይለማርያም ከፍያለው እንዳሉት÷ በክልሉ በተያዘው ዓመት ከ41 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በበጋ መስኖ ስንዴ ተሸፍኗል።
 
በዚህም ከ2 ሚሊየን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅ ነው የገለጹት፡፡
 
አርሶ አደሮች በጦርነቱ የታጣውን ሰብል ለማካካስ በተደረገው ጥረት የራሳቸውን ድርሻ መወጣታቸውን ዶክተር ኃይለማርያም ተናግረዋል።
 
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈጉባዔ አማረ ሰጤ በበኩላቸው÷ በጦርነት ውስጥ ሆኖም ቢሆን ክልሉ ባሉት ዞኖች ውስጥ የልማት ሥራዎችን ማከናወኑ የሚበረታታ መኾኑን ገልጸዋል።
 
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተያዘው ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ2 ሺህ 600 ሄክታር መሬት በላይ በዘር የተሸፈነ ሲሆን÷ ከ100 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመላክቷል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.