አሸባሪው ህወሓት በየጊዜው በሚያደርገው ትንኮሳ የተፈናቀሉ ዜጎችን ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ የማስፈር ስራ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በየጊዜው በሚያደርገው ትንኮሳ የተፈናቀሉ ዜጎችን ደህንነቱ በተጠበቀ መጠለያ የማስፈር ስራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡
የኮሚሽኑ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ አሸባሪው እና ወራሪው የህወሓት ቡድን በየጊዜው በሚያደርገው ትንኮሳ ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ምቹ በሆነ ስፍራ የማስፈሩ ሂደት በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ ነው፡፡
አሁን ላይ የጥፋት ቡድኑ በሚያካሂደው ትንኮሳ የተፈናቀሉ 56 ሺህ 701 ዜጎች በራያ ቆቦ ከተማ በአምስት መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ የሚገኙ ተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ እነዚህን ዜጎች በሌላ ቦታ ማስፈር በማስፈለጉ የተለያዩ ተቋማት የተካተቱበት ኮሚቴ የቦታ መረጣ ስራ ማከናወኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ ጃራ ቀበሌ ለተፈናቃዮች መጠለያ የሚሆን ቦታ መለየቱን ነው አቶ ደበበ የገለጹት፡፡
ወደ መጠለያው ለሚገቡ ዜጎች አስፈላጊው ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁስ እየቀረበ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ለመጋዝን፣ ለጤና ማዕከል እና ሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ስፍራዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፥ለተፈናቃዮች መጓጓዣ እና ሌሎች ወጪዎች ኮሚሽኑ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
ዜጎችን ወደየመጠለያ ጣቢው በማዛወሩ ሂደት የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን፣ የሰሜን ወሎ ዞን ምግብ ዋስትና መምሪያ፣ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ በዞኑ የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና መከላከያ ሚኒስቴር መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች፣ የሀገር ውስጥ ተቋማት እና ባለሃብቶች በመጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያደርጉም ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!