Fana: At a Speed of Life!

የፈተናዎች ኤጀንሲ ለቀረቡለት ከ20 ሺህ በላይ የተማሪ ቅሬታዎች ምላሽ መስጠቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የፈተና ውጤትን አስመልክቶ ለቀረቡለት ከ20 ሺህ በላይ የተማሪዎች ቅሬታዎች ምላሽ መሰጠቱን የፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ ከፈተና እርማት እና ቅሬታዎች ጋር በተያያዘ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው፥ የፈተናው እርማት ከሰው ንክኪ ነፃ በሆነ መልኩ በጥንቃቄ የተከናወነ ቢሆንም በሁለተኛው ዙር ፈተና እርማት ላይ የቴክኒክ ችግር ማጋጠሙን እና ማስተካከያ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

የእርማት ችግሩ የተፈጠረው ከ559 ባልበለጡ ተማሪዎች ላይ እንደሆነ እና ችግሩን ለመፍታት ዳግም ምልከታ ተደርጎ የማስተካከያ ስራ መሰራቱን ነው የገለጹት፡፡

የፈተና እርማት ችግር ማጋጠሙ የታወቀውም የፈተናዎች አገልግሎት ባደረገው ምርመራ እንደሆነ ተናግረው፥ ቅሬታዎችን በተመለከተም ተማሪዎች ሳይጉላሉ ባሉበት ቦታ ሆነው ቅሬታቸውን ለመፍታት የሚያስችል ስርዓት ተዘርግቶ ችግሩ መስተካከሉን አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሰረት ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎች ቅሬታቸውን አቅርበው ምላሽ መሰጠቱንም ነው የተናገሩት፡፡

በተደጋጋሚ የሚነሱ የፆታ እና የስም ስህተቶች በትምህርት ቤቶች አካባቢ የተፈጠሩ ክፍተቶች እንጂ የፈተናዎች አገልግሎት ክፍተት አለመሆኑንም ዳይሬክተሩ መግለፃቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በዘንድሮው የተፈታኝ ተማሪዎች መብዛት እና በአገራችን ውስጥ ካሉት 47 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አሁን 43ቱ ተቋማት ብቻ የሚቀበሉ በመሆኑ እና ይህም የዩኒቨርስቲዎች የቅበላ አቅም አነስተኛ እንዲሆን በማድረጉ የመግቢያ ነጥቡን ከፍ እንዲል እንዳደረገው ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.