ከባህር ዳር – ዳንግላ በሚሄድ 66KV አስተላለፊ መስመር በተፈፀመ ስርቆት የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጧል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከባህር ዳር – ዳንግላ በሚሄድ 66KV አስተላለፊ መስመር በተፈፀመ ስርቆት ዳንግላ፣ ዱርቤቴ፣ መራዊ ፣ ኮሶበር፣ ግምጃ ቤት፣ ቻግኒ እና በአካባቢያቸው ባሉ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጧል፡፡
የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዳሳወቀው÷ ከባህር ዳር እስከ ዳንግላ በሚሄድ 66 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ አስተላለፊ መስመር የብረት ታወር ላይ በተለምዶ “ቆጥቆጥማ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተፈፀመ ስርቆት ምሰሶዎች በመውደቃቸው ከዳንግላ እና ፓዌ ማከፋፈያ ጣቢያ ኤሌክትሪክ የሚያገኙ ከተሞች ኃይል ተቋርጧል፡፡
በተፈፀመው ስርቆት ምክንያት አራት የብረት ታወሮች የወደቁ ሲሆን÷ የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የእንጨት ምሰሶዎችን በመቀየር አገልግሎቱን ወደነበረበት ለመመለስ ርብርብ ያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡
በብረት ታወሮች እና በአጠቃላይ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ እየተፈፀመ ያለው ስርቆት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባበሰ የመጣ በመሆኑ÷ በአገልግሎት አሰጣጣችን ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት ፈጥሮብናል ብሏል አገልግሎቱ፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡና በየደረጃው የሚገኝ የፀጥታ አካል በአካባቢው የተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በንቃት እንዲጠብቅና ከዚሁ ጋር በተያያዘ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለሚመለከተው የፀጥታ አካልና ለተቋሙ እንዲጠቁም አገልግሎቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡