የመመሪያ ጥሰት በፈጸሙ 7 የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የማስተካከያ እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመመሪያ ጥሰት በፈጸሙ ሰባት የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የማስተካከያ እርምጃ መውሰዱን የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ የኅብረተሰቡን ጥቆማዎች መነሻ በማድረግ ተቋማት ላይ ባካሄደው ድንገተኛ ጉብኝት በሰባት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካምፓሶች ላይ የእርምት እርምጃዎች መውሰዱን አስታውቋል።
የማስተካከያ እርምጃ የተላለፈባቸው ተቋማት(ካምፓሶች) ዝርዝርም እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
1. ቢ ኤስ ቲ ኮሌጅ ጊንጪ ካምፓስ ፡- በጊንጪ ከተማ ከባለስልጣኑ የእውቅና ፈቃድ ሳይሰጠው በድህረ ምረቃ እና በቅድመ ምረቃ ደረጃ ተማሪዎችን መዝግቦ እያስተማረ በመሆኑ የከፈተውን ካምፓስ በመዝጋትና የመዘገባቸውን ተማሪዎች በማሰናበት ለባለስልጣኑ በ10 ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርግ እና በጊንጪ ከተማ በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ እስከ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ለመሰማራት እንዳይችል እግድ ተጥሎበታል፡፡
2. ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ሆሳዕና ካምፓስ፡- በሆሳዕና ከተማ ከባለስልጣኑ የእውቅና ፈቃድ ሳይሰጠው ተማሪዎችን መዝግቦ እያስተማረና በቅድመ ምረቃ ደረጃ የመግቢያ መስፈርት የማያሟሉ ተማሪዎችን መዝግቦ እያስተማረ በመገኘቱ ያለእውቅና ፈቃድ በድህረ ምረቃ ደረጃ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የከፈተውን የትምህርት መስክ በመዝጋት የመዘገባቸውን ተማሪዎች በማሰናበት በ10 ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርግ እና በሆሳዕና ከተማ በድህረ ምረቃ ደረጃ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን እስከ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ለመሰማራት እንዳይችል እግድ ተጥሎበታል፡፡
3. ግሬት ቪዥን ኮሌጅ ሆሳዕና ካምፓስ፡- በሆሳዕና ከተማ ከባለስልጣኑ በድህረ ምረቃ ደረጃ የእውቅና ፈቃድ ሳይሰጠው በፕሮጀክት ማኔጅመንት ተማሪዎችን መዝግቦ እያስተማረ በመገኘቱ በድህረ ምረቃ ደረጃ በፕሮጀክት ማኔጅመንት የከፈተውን የትምህርት መስክ በመዝጋትና የመዘገባቸውን ተማሪዎች በማሰናበት ለባለስልጣኑ በ10 ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርግ እና በሆሳዕና ከተማ በድህረ ምረቃ ደረጃ በፕሮጀክት ማኔጅመንት እስከ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ለመሰማራት እንዳይችል እግድ ተጥሎበታል፡፡
4. ዛክቦን ኮሌጅ ሻሸመኔ ካምፓስ ፡- በሀላባ ከተማ ከባለስልጣኑ በቅድመ ምረቃ ደረጃ በመደበኛ መርሃ ግብር በኢኮኖሚክስ እና በአካውንቲንግ ኤንድ ፋይናንስ እንዲሁም በቅድመ ምረቃ ደረጃ በርቀት መርሃ ግብር በቢዝነስ ማኔጅመንት የከፈተውን የትምህርት መስክ በመዝጋትና የመዘገባቸውን ተማሪዎች በማሰናበት ለባለስልጣኑ በ10 ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርግ እና በሀላባ ከተማ በቅድመ ምረቃ ደረጃ በመደበኛ መርሃ ግብር በኢኮኖሚክስ እና በአካውንቲንግ ኤንድ ፋይናንስ እንዲሁም በቅድመ ምረቃ ደረጃ በርቀት መርሃ ግብር በቢዝነስ ማኔጅመንት እስከ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ለመሰማራት እንዳይችል እግድ ተጥሉሎበታል፡፡
5. ብርሃን ኮሌጅ ደብረ ብርሃን ካምፓስ ፡- በሸዋሮቢትና በተለያዩ የሰሜን ሸዋ ከተሞች ከባለስልጣኑ የእውቅና ፈቃድ ሳይኖረው በድህረ ምረቃ ደረጃ ተማሪዎችን መዝግቦ እያስተማረና በደብረ ብርሃን ካምፓሱ በቅድመ ምረቃ ደረጃ የመግቢያ መስፈርት የማያሟሉ ተማሪዎችን መዝግቦ እያስተማረ በመገኘቱ የከፈተውን ካምፓስ በመዝጋትና የመዘገባቸውን ተማሪዎች በማሰናበት ለባለስልጣኑ በ10 ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርግ እና በሸዋሮቢት ከተማ በድህረ ምረቃ ደረጃ እስከ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ለመሰማራት እንዳይችል እግድ ተጥሎበታል፡፡
6. ዮም የድህረ ምረቃ ኮሌጅ ሀዋሳ ካምፓስ ፡- በሆሳዕና ከተማ ከባለስልጣኑ የእውቅና ፈቃድ ሳይሰጠው የማስተማሪያ ቦታ ለውጥ በማድረጉ የጽሁፉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል ፡፡
7. ለራዳ ኮሌጅ ደብረ ብርሃን ካምፓስ ፡- በደብረሲና ከተማ ከባለስልጣኑ እውቅና ባልሰጠበት አግባብ የደረጃ ስያሜ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የደረጃ ስያሜ በመጠቀሙ የጽሁፉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል፡፡ የልተፈቀደለትን የደረጃ ስያሜ እስከ ሚያዝያ 03/2014 ዓ.ም ማስተካከያ አድርጎ ለባለስልጣኑ ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡