በአፍሪካ እና አውሮፓ ህብረት የጋራ ጉባኤ ኢትዮጵያ ያነሳቻቸው ሀሳቦች ተቀባይነት አግኝተዋል- አምባሳደር ሂሩት ዘመነ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ6ኛው የአፍሪካ እና አውሮፓ ህብረት የጋራ ጉባኤ ኢትዮጵያ ያነሳቻቸው በርካታ ሀሳቦች ተቀባይነት ማግኘታቸውን በቤልጂየም፣ ሉክሰንበርግና በአውሮፓ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ገለጹ።
አምባሳደሯ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከጉባኤው ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በጋራ ጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ ያነሳቻቸው የትብብርና የአጋርነት ሁኔታ፣ በሰላምና ጸጥታ ጉዳይ የአፍሪካ ድምጽ ስለሚሰማበት እንዲሁም የወቅቱን የአፍሪካ ህብረት መሪ ቃል የተመለከቱ ጉዳዮች ተቀባይነት እንዳገኙ ጠቁመዋል።
የአፍሪካና የአውሮፓ ህብረት ግንኙነት በእኩልነትና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብር እንዲሆን ኢትዮጵያ ማንሳቷን ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከተለያዩ አገሮች መሪዎች ጋር በነበራቸው የጎንዮሽ ውይይት÷ በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለው ግንኙነት መጠናከር ስለሚኖርበት ሁኔታ ምክክር ተደርጓልም ነው ያሉት።
በዚህም ለስድስት ወር የአውሮፓ ህብረት ሊቀመንበር ከነበረችው ስሎቬኒያ እና አሁን ሊቀመንበርነቱን ከተረከበችው ፈረንሳይ መሪዎች ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መወያየታቸውን አስታውሰዋል።
በጉባኤው የአፍሪካ ድምጽ በሰላምና ጸጥታ፣ ድህነትን በመዋጋት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመቀነስ፣ የታዳሽ ሃይል ልማትን በማጠናከር እንዲሁም በስደተኞች ጉዳይ የአህጉሩንና የኢትዮጵያን መብት ባስጠበቀ መልኩ ተነስቶ የጋራ መግባባት እንደተደረገበት አምባሳደሯ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መጠናከር ለቀጣናው መጠናከር ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሯ፥ በችግር ውስጥ ሆና የልማት ትልሟን ለማሳካት እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በመስኖ ልማት፣ በበጋ የስንዴ ልማት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በአረንጓዴ ልማትና በመሳሰሉት ሰፊ ርብርብ እያደረገች የምትገኘው ኢትዮጵያ እውነቷን ለማስረዳት መቻሏን ጠቁመዋል።
በተለይም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል አጋጥሞ የነበረው ጦርነት ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበት መሆኑን ማስገንዘብ መቻላቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!