የጀጎል ግንብን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ እየተዋበ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የጀጎል ግንብ ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የማስዋብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የ የሐረሪ ክልል ባህል፣ ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጀጎል ግንብ ከንጽህና ጋር በተያያዘ ለጉዳት እየተዳረገ መምጣቱን በቢሮው የቋንቋ ዳይሬክተር አቶ ጃሚ መሃመድ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም “ጀጎልን ጽዱ እና ውብ እናድርጋት” በሚል መሪ ሀሳብ በጀጎል የሚገኙ የአሚር ኑር እና አባድር ወረዳዎችን በማስተባበር እና የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
“የተባበረ ክንድ አንድ ላይ ለውጥ ያመጣል” በሚል እምነት ሁለቱ ወረዳዎች ከክልሉ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን ህብረተሰቡን በማስተባበር ጀጎልን የማስዋብ ሥራ እየሰራን እንገኛለን” ያሉት ደግሞ የአሚር ኑር ወረዳ የከተማ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አሚር ረመዳን ናቸው።
ጀጎልን ማሳመር ጥቅሙ የሁሉም መሆኑን የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ በበኩላቸው ፥ ህብረተሰቡ ተባብሮ ጀጎልን ወደ ቀድሞ ታሪካዊ ውበቱ ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተገነባ የሚነገርለት የጀጎል ግንብ አምስት በሮች ያሉት ሲሆን÷ በውስጡም ከሚገኙት ታሪካዊ ቅርሶች መካከል ረጅም እድሜ ያስቆጠሩ መስጊዶችና የፈረንሳዊው ጸሐፊ የአርተር ራንቡ መኖሪያ ቤት ይጠቀሳሉ።
ሙዚየሞች፣ የሐረሪ ባህላዊ ቤቶች፣ የጅብ ምገባ ትርዒት ማሳያ ስፍራ እንዲሁም ሌሎች ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ጥንታዊ የመስህብ ስፍራዎች እንደሚገኙ ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!