ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከአፋር ህዝብ ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል እየፈጸመ ያለውን ጥቃት ለመከላከል እና በገባበት ለማስቀረት የአፋር ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻና ህዝባዊ ሰራዊት እየተፋለመ መሆኑን የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ሃላፊው አቶ አህመድ ካሎይታ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ቡድኑ በተለያዩ ጊዚያት የአፋርን ህዝብ ለመጉዳት ጦርነት ከፍቶ ሃብትና ንብረትን ከማውደም ጀምሮ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ዋጋ እያስከፈለ ነው።
አሸባሪው ቡድን ለመዝረፍ እና ለማዋረድ እያደረገ ያለውን ወረራና ጥቃት የተረዳው የክልሉ ህዝብ ተቀናጅቶና ተናቦ ህልውናውን ለማስከበር አልፎም የሽብር ቡድኑን ዓላማ ለማምከን በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ሃላፊው አመላክተዋል።
አፋር በታሪኩ ማንነቱን እና ክብሩን ለጠላት አሳልፎ ላለመስጠት ብዙ መስዋዕትነትን ሲከፍል ቆይቷል ያሉት ሃላፊው ፥ ንጹሃንን፣ ሴቶችን፣ አዛውንቶችንና ህጻናትን በጭካኔ የጨፈጨፈ ጠላት ግን ገጥሞት አያውቅም ብለዋል።
የአፋር ህዝብ ንጹሃንን ዒላማ አድርጎ ጥቃት እያደረሰ ያለውን አሸባሪ ቡድን ለመዋጋት እና የራሱን መብትና ህልውና በራሱ ለማስከበር ወደ ትግል እንዲገባ አድርጎታል ሲሉም ተናግረዋል።
የዕለት ኑሯቸውን የሚከውኑ ንጹሃን አርብቶ አደሮችን ሳይቀር በግፍ መግደል እና በማፈናቀል ቡድኑ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ገልጸው ፥ ከማውደምም ባለፈ የአርብቶ አደሩን ንብረት እየዘረፈና ለራሱ የምግብ ፍጆታ እያዋለ ነውም ብለዋል።
አሁን ላይ በሁሉም ግንባሮች የአፋር ህዝብ እራሱን እየተከላከለ እና እየታገለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ለክልሉ እየተደረገ ያለውን ድጋፍ ሁሉም ተባባሪ በመሆን ከአፋር ህዝብ ጎን ሊቆም እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በክልሉ የሽብር ቡድኑን ሃሳብ ለመደገፍ በተሳሳተ መንገድ ተታለው የነበሩ አካላትን በቂ ግንዛቤ በማስጨበጥ የህዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል ስልጠና እየተሰጣቸው ነውም ተብሏል።
ህዝቡ ላይ የደረሰውን በደል በመገንዘብ ከአፋር ህዝብ ጎን ቆመው አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆን መቻላቸውንም አቶ አህመድ ገልጸዋል ።
በይስማው አደራው፣ አብራሂም ሙሳና ሰዓዳ ጌታቸው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!