ፈረንሳይ በማሊ ያሰማራቻቸውን ወታደሮቿን ልታስወጣ ነው
አዲስ አበባ፣የካቲት 10፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈረንሳይ በማሊ ለፀረ-ሽብር ዘመቻ ያሰማራቻቸውን ወታደሮቿን ልታስወጣ መሆኑን አስታውቃለች፡፡
ውሳኔዉ በፈረንሳይ እና በአጋሮቿ የተፈረመ ሲሆን፥ በተለይም ማሊን የተቆጣጠረዉ ወታደራዊ ሀይል ከፈረንሳይ ጋር በወታደራዊ ዘርፎች ላይ ለመስራት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የተወሰነ ነው ተብሏል፡፡
በዚህም በማሊ እና በሰሀል ቀጠና ውስጥ ከሚገኙ ታጣቂዎች ጋር በሚደረገው ውጊያ ላይ እገዛ ሲያደርጉ የነበሩት ፈረንሳይ እና አጋሮቿ ወታደራዊ ሀይላቸውን ከቀጠናው ለማስወጣት መወሰናቸው ተመላክቷል፡፡
አሁን ላይ የፈረንሳይ ወታደሮች ማሊን በመልቀቅ በኒጀር እና በጊኒ ባህረ ሰላጤ እስከ ሰኔ 2022 ለመቆየት እቅድ እያወጡ ስለመሆኑም ቲ አር ቲ ወርልድ በዘገባው አስፍሯል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፥ የማሊ ወታደራዊ መንግስት ፖለቲካዊ አቋም ፈረንሳይን ከቀጠናዉ ለቃ እንድትወጣ አስገድዷታል፤ ለአስር አመታት ያህል የዘለቀው የሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ስምምነትም ፍሬ አልባ ሆኖ ተጠናቋል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል የማሊ ወታደራዊ መንግስት ፈረንሳይ ለፀረ-ሽብር ተልዕኮ ባሰማራቻቸዉ ወታደሮቿ በቀጠናዉ የሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎችን እየረዳች ነው በሚል ወታደሮቿን ከቀጠናዉ እንድታስወጣ መጠየቁ የሚታወስ ነው፡፡
በሰሀል ቀጠና በአጠቃላይ 25 ሺህ ወታደሮች ተሰማርተው የነበረ ሲሆን፥ 4 ሺህ 300 የሚሆኑት ደግሞ የፈረንሳይ ወታደሮች ናቸዉ።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!