Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ምክር ቤት አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ለውጡ የወለደውን አመለካከትና አስተሳሰብ በአግባቡ የተንሸራሸረበት ነው-አቶ ዮናስ ዘውዴ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ለውጡ የወለደውን አመለካከትና አስተሳሳብ በአግባቡ የተንሸራሸረበት መሆኑን የአስተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮናስ ዘውዴ ገለጹ።
ኃላፊው የጉባኤው ሂደት አስመልክተው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስረዱት፥ ጉባኤው ባለፉት ስድስት ወራት የመልካም አስተዳደርና ልማት እቅዱ አፈፃፀም፣የህልውና ዘመቻ፣የሰላምና ጸጥታ ጨምሮ ሌሎችም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተዳሰሱበት ነው።
በዚህም ለውጡ የወለደውን አመለካከትና አስተሳሰብ ከማቀናጀት አንፃር ውጤት የታየበትና ሀሳብም በነጻነት የተንሸራሸረበት ነው ብለዋል።
የመሬት፣የኑሮ ውድነት፣የመኖሪያ ቤት ፣ መብራት፣ውሃና የመንገድ መሰረተ ልማትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ከምክር ቤት አባላት ተነስተው በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ መሰጠቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት፣የተማሪዎች ምገባ፣ጤናና ሌሎች ጥያቄዎች ተነስተዋል ያሉት አቶ ዮናስ፥ይህንን በአግባቡ በማስተናገድ ምክር ቤቱ ትክክለኛ ለውጥ የታየበት እንደሆነ ተናግረዋል።
ወደ ምክር ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርጠው መግባታቸውን ያወሱት ኃላፊው ፥ ከዚህ በፊት ከነበሩት ምክር ቤቶች ፈፅሞ የተለየ የህዝብ ወገንተኝነትና ሃላፊነት ለመወጣት ቁርጠኝነት የታየበት እንደሆነ መታዘባቸውን አስረድተዋል።
የህዝቡ እሮሮ፣ብሶትና መሰረታዊ ጥያቄዎች የተነሱበት ጉባኤ መሆኑን ጠቅሰው፥ አስተዳደሩ ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸውና የተገኙ ውጤቶች ተጠናክሮ እንዲቀጥል የምክር ቤቱ ድጋፍ፣ክትትልና እገዛ ወሳኝ መሆኑንም አብራርተዋል።
የመደመር አስተሳሰብና አመለካከት የብልጽግና ጉዞን ወደፊት በማራመድ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ተምሳሌት ለማድረግ ነው ብለዋል።
ከህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ጀምሮ ሀገራችን እንደ ሀገር ያለፈችበትን ሁኔታ የዳሰሰ ጉባኤ ነበር ያሉት አቶ ዮናስ ፥ አዲስ አበባ ተከባለች ለቃቹ ውጡ፣ሂዱ እየተባለ በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ማህበረቡ ስጋት ላይ ለመጣልና አመራሩ እንዲሸሽ የተደረገው የውጭ ሃይሎች ጫናን የመከነ አስተማማኝ ሰላም በመዲናዋ እንደነበር ያረጋገጠ ኩነት መሆኑንም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ህዝብ በጣም በሚያስደንቅ ሁኔታ የህልውና ዘመቻውን በገንዘብና በዓይነት ከመደገፍ ባለፈ የከተማዋ ወጣቶች የመከላከያ ሠራዊቱን በመቀላቀል ጠላትን ከፊት ለፊት በመጋፈጥ የፈፀሙት ተግባር በጉባኤ ከተነሱ ነጥቦች መካከል ናቸው ብለዋል።
ወጣቶች የከተማዋን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ 24 ሰዓት ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ተቀናጅተው እንደሰሩ የገለጹት ኃላፊው ፥ የከተማዋ ባለሃብቶች 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለህልውና ዘመቻ ድጋፍ ማድረጋቸውንም አውሰተዋል።
35ኛው የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባኤ በመዲናዋ መካሄዱ አዲስ አበባ ሰላም መሆኑን የሚያረጋግጥ ከመሆኑንም ባለፈ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ክፉ ምኞች በማምከን ረገድ ትልቅ መልዕክት ያስተላለፈ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪ የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ያመረና የተሳካ እንዲሆን ከተማዋን በፅዳትና በማስዋብ፣በአገልግሎት፣በትራንስፖርት፣በሰላምና ፀጥታ አጠባበቅ ላይ ያደረጉት የተቀናጀ ርብርብ የሚያስመሰግንና አንዳችን ለሌላችን የምናስፈልግ መሆኑን የተገነዘብኩበት ነው ሲሉ አቶ ዮናስ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.