ወጣት ስራ አጥ ሀኪሞችን ቁጥር ለመቀነስ እየተሰራ ነው ተባለ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ወጣት ሀኪሞችን በማብቃት የጤና አገልግሎቱን ማጎልበት በሚል መሪ ቃል 56ኛው ዓመታዊ የህክምና ጉባኤ እና ዓለም አቀፍ የጤና አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ ወጣት ስራ አጥ ሀኪሞችን ወደስራ ለማስገባት ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በክልል ያሉ ስፔሻሊስት ሀኪሞች ደመወዝ በፌደራል መስሪያ ቤት እንዲሸፈንና ክልሎች ለዚህ የሚይዙትን በጀት ለአዳዲስ ሀኪሞች እንዲያውሉ የሚያደርግ የመፍትሄ አቅጣጫ ተቀምጧልም ነው ያሉት።
ከዚህ ባለፈም በጤና ጣቢያዎች ሀኪሞችን በመመደብ የህክምና አገልግሎቱን በማሻሻል ለወጣት ሀኪሞች ስራ መስጠት የሚያስችል መፍትሄ መቅረቡንም ገልጸዋል።
ለሶስት ቀናት የሚቆየው አውደ ርዕይ ወጣት ሀኪሞችን ማብቃትና የጤና አገልግሎቱን ማጎልበት በሚቻልበት መንገድ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይመክራል።
ከዚህ ባለፈም ከሀገር ውስጥ የተሻገረ የህክምና ቱሪዝምን መፍጠር እና ስራ ጠባቂ ሳይሆን ስራ ፈጣሪ ሀኪሞችን እንዴት እንፍጠር በሚሉ አጀንዳዎች ላይ ይመክራል ተብሎም ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ጠንካራ እና ታማኝ ሀኪም ለተሻለ ጤና ብሎ በ1954 ዓ.ም የተመሠረተ የሀገሪቱ የመጀመሪያ የሙያ ማህበር ነው።
በመታገስ አየልኝ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision