Fana: At a Speed of Life!

በጸጥታ ችግር ምክንያት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ላልወሰዱ ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው ፈተና ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በጸጥታ ችግር ምክንያት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ላልወሰዱ ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው ፈተና በሰላም መጠናቀቁን የየክልሎቹ ትምህርት ቢሮዎች አስታወቁ፡፡
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ ክልል በከፈተው ወረራ የመጀመሪያውን ዙር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ላልወሰዱ ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው ሁለተኛ ዙር ፈተና በሰላም መጠናቀቁን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
ፈተናው በ6 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ በ129 የፈተና ጣቢያዎች ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
በቢሮው የፈተና ዝግጅት እና አስተዳደር ተወካይ ቡድን መሪ ኃይሉ ታምር ለአሚኮ እንደገለጹት÷ ሁለተኛውን ዙር ብሔራዊ ፈተና መውሰድ ከነበረባቸው ተማሪዎች መካከል 97 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች ምዘናውን ወስደዋል፡፡
በአካባቢው ባለ ወቅታዊ ችግር ምክንያት በጠለምት ደጃች ሜዳ፣ አዲአርቃይ እና አበርገሌ አካባቢዎች ምዘናው እንዳልተሰጠም ተናግረዋል፡፡
ምዘናውንም ከ2014 ዓ.ም ተማሪዎች ጋር በጋራ የሚወስዱበት መንገድ ይመቻቻል ብለዋል፡፡
ምዘናው በተሰጠባቸው ጣቢያዎች ፈተና ያልወሰዱ ተማሪዎች ችግራቸው እየታየ በቀጣይ ከሚፈተኑ ተማሪዎች ጋር የሚስተናገዱበት መንገድም ይመቻቻል ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት በ2013 ዓ.ም ፈተና መውሰድ ያልቻሉ ተማሪዎች ከጥር 24 እስከ 27 ቀን 2014 እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ እንዳስታወቀው፥ ለአራት ቀናት ሲሰጥ የነበረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በሰላም ተጠናቋል፡፡
ፈተናውን ለመውሰድ ከተመዘገቡት 21 ሺህ 202 ተማሪዎች ውስጥ 18 ሺህ 955 ተማሪዎች ፈተና መውሰዳቸውን ቢሮ ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.