Fana: At a Speed of Life!

የወሎ፣ የመቅደላ አምባና የወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች በየካቲት ወር ዳግም ስራ ይጀምራሉ – የትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ህወሓት ዘረፋና ውድመት የተፈፀመባቸው የወሎ፣ የመቅደላ አምባና የወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ተማሪዎችን በመቀበል ዳግም ስራ የሚጀምሩ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ለኢዜአ እንደገለጹት ፥ በአማራ ክልል አሸባሪው ህውሓት በከፈተው ጦርነት ሳቢያ የወሎ፣ የመቅደላ አምባና የወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ስራ አቋርጠዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው ወራት ዩኒቨርሲቲዎቹን ዘርፎና አውድሞ መሄዱን አስታውሰው ፥ በዳግም ጥገና ስራ እንዲጀምሩ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

በመንግስት ድጋፍና ባላቸው አቅም አስፈላጊ ግዢዎችንና ጥገናዎችን እንዲያካሔዱ ከማድረግ ባለፈ አማራጭ የትምህርት ማስኬጃ መንገዶችንም እንዲያስቡና ወደ ስራ እንዲገቡ አሁንም ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በመሆኑም የወሎ፣ የመቅደላ አምባና የወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ተማሪዎችን በመቀበል ዳግም ስራ የሚጀምሩ መሆኑን ዶክተር ሳሙኤል ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ የመጨረሻ ዓመት ተመራቂ ተማሪዎችን ቀድመው በመቀበል ሌሎችንም በሚያወጡት መርሃ ግብር መሰረት የሚቀበሉ ይሆናል።

በአሸባሪው ህወሓት ወረራ እና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ ተዛብቶ የቆየው የአካዳሚክ ካሌንደር በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ይስተካከላል ብለዋል ዶክተር ሳሙኤል።

የአካዳሚክ ካላንደሩን በማስተካከል በዩኒቨርሲቲዎች የተሳካ የመማር ማስተማር ሂደት እውን ለማድረግ አጠቃላይ የትምህርት ማህበረሰቡ፣ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ሌሎችም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.