ከፍተኛ አመራሩ በተገኘው ድል ሳይኩራራ በቀጣይ ሊያጋጥሙ ለሚችሉ ፈተናዎች ተግቶ እንዲዘጋጅ ጠ/ሚ ዐቢይ አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ተቋማትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲያካሂዱ የነበረውን ውይይት አጠናቀቁ።
የመንግስት ከሚኒኬሽን አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ በዘመቻ ህብረ-ብሄራዊ አንድነት በተገኙ ድሎች፣ በታዩ ውስንነቶችና በቀጣይ ስለሚኖረዉ አቅጣጫ አስመልክቶ ባለፉት ሦስት ቀናት ውይይት ሲካሄድበት የቆየው የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ግምገማዊ ሥልጠና በዛሬው እለት ተጠናቋል።
ከፍተኛ አመራሮቹ በውይይታቸው በጦርነት የሚገኝ ድልን በአግባቡ መምራት ከጦርነቱ በኋላ ለሚመጣ መረጋጋትና ሰላም እንዲሁም ለዘላቂ የሀገር ግንባታ ሂደት ትልቅ ፋይዳ እንዳለዉ አስምረውበታል፡፡
በዘመቻውም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ድል ማድረገቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የህልውና ዘመቻው ያስከተለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እጅግ አሳዛኝና የሀገር እዳ ቢሆንም ሂደቱ ግን በርካታ ትሩፋቶችን እንዳስገኘ አመራሩ መገምገሙ ተመልክቷል፡፡
ተናብቦና ተቀናጅቶ በአንድ አመራር ለአንድ ዓለማ የመስራት አቅም፣ ህብረ-ብሄራዊ አንድነትና ሁለንተናዊ ህዝባዊ ተሳትፎና ተደጋግፎ ችግሮችን በጋራ መሻገርን እንዳስገኘ አመራሮቹ በግምገማ አዘል ስልጠናቸው ማረጋገጣቸው ተመልክቷል፡፡
አመራሮቹ ከድሎቹ ጋር የታዩና ቀጠይም ሊኖሩ ስለሚችሉ መልካም እድሎችና ዝንፈቶችን በትኩረት ገምግመዋል፡፡
በጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደው የማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዘመቻ ለኅብረ ብሄራዊ አንድነት የመጀመሪያው ምእራፍ በስኬት እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸው ለዚህም ላቅ ያለ ተሳትፎና አበርክቶ ምስጋና አቅርበዋል።
በተገኘው ድል ሳንኩራራ በቀጣይ ሊያጋጥሙን ለሚችሉ ፈተናዎች ተግተን መዘጋጀት እንደሚገባንም አሳስበዋል። የኢትዮጵያን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስብራቶች ለመጠገን የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስምረውበታል፡፡
በየደረጃዉ ያለው አመራርም በጦርነቱ ጫና የደረሰበትን የብልፅግና ጉዟችንን ለማስቀጠል ታሪካዊ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በዘመቻው የተገኘውን የኅብረ ብሄራዊ አንድነት ስሜት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ሁለንተናዊ ብልጽግናችንን ለማረጋገጥ እንድንጠቀምበት ጥሪ አቀርባለውም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!