የወደሙ ጤና ተቋማትን ከሆስፒታሎች ጋር በማስተሳሰር አገልግሎት ለማስጀመር ስራ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ህወሓት ውድመትና ዘረፋ የተፈጸመባቸውን የጤና ተቋማት አገልግሎት ወደነበረበት ለመመለስ የአዲስ አበባና የፌዴራል ሆስፒታሎች የድርሻቸውን መወጣት መጀመራቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
አሸባሪው የጥፋት ቡድን ካደረሰው ጉዳት ጋር ተያይዞ በሰሜናዊው የሀገሪቱ ክፍል በሺዎች የሚቆጠሩ የጤና ተቋማት የወደሙ ሲሆን እነዚህን የጤና ተቋማት ወደነበሩበት ለመመለስ እና አገልግሎት እንዲሰጡ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
በዚሁ መሰረት በግጭቱ ምክንያት የወደሙ ጤና ተቋማትን ወደነበሩበት ለመመለስና የጤና አገልግሎት ለማስጀመር የአዲስ አበባ ጤና ቢሮና የፌዴራል ሆስፒታሎችን ከወደሙ ሆስፒታሎች ጋር በማስተሳሰር ድጋፍ እንዲያደርጉ ሰፊ ስራ መጀመሩንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በቀጣይም ሌሎች ክልሎች እና ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎችን በማስተባበር የድጋፍ ስራው በስፋት እንዲቀጥል ይደረጋልም ነው ያለው።
በአሁኑ ሰዓት ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ደሴ ሆስፒታልን፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከልዋን ሆስፒታልን እና ቦሩ ሜዳ ሆስፒታልን፣ አቤት ሆስፒታል ባቲ ሆስፒታልን፣ የካቲት 12 ሆስፒታል ወረኢሉ ሆስፒታን፣ ምኒሊክ ሆስፒታል መሃል ሜዳ ሆስፒታልን፣ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ከሚሴ ሆስፒታልን፣ ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሀይቅ ሆስፒታልን፣ ራስ ደስታ ሆስፒታል ደብረ ሲና ሆስፒታል ጋር ትስስር በመፍጠር ወደ ስራ ገብተዋል ብሏል።
ከዚህ ባለፈም አለርት ሆስፒታል ኮምቦልቻ ሆስፒታልን፣ ዘውዲቱ ሆስፒታል ደጎሎ ሆስፒታልን፣ ጋንዲ ሆስፒታል ሞላሌ ሆስፒታልን፣ አማኑኤል ሆስፒታል የአእምሮ ጤናና የስነልቦና ማህበራዊ አገልግሎት ድጋፍ ለሁሉም ሆስፒታሎች ከላይ በተገለጸው መሰረት የአዲስ አበባና ፌዴራል ሆስፒታሎች ትስስር በመፍጠር ወደ ድጋፍ ስራው መግባታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።
ሆስፒታሎቹን ሙሉ ለሙሉ ወደነበሩበት ለመመለስ አሁንም ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይና ድጋፍ ስለሚያስፈልግ ሁሉም አካል ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርቧል።