Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) አመራሩ በይበልጥ የአገልጋይ አመራር ሰብዕና ተላብሶ እንዲሠራ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ የመሻገር ትልሞችን በቅንጅት በማሳካት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር አመራሩ የአገልጋይ አመራር ሰብዕና ተላብሶ እንዲሠራ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳሰቡ።

ብልጽግና ፓርቲ ላለፉት 12 ቀናት በአዳማ ያካሄደው የከፍተኛ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቅቋል።

ፓርቲው “የህልም ጉልበት ለእመርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሐሳብ ከክልሎች፣ ከተማ አሥተዳደሮችና ከፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ ከ2 ሺህ በላይ ከፍተኛ የአመራር አባላቱ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ስልጠናውም የነገዋን ኢትዮጵያ ብልጽግና በማረጋገጥ የትውልዱን መፃኢ እድል ምቹና ስኬታማ ማድረግ በሚያስችሉ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባላቸው ሐሳቦች ዙሪያ ያተኮረ መሆኑን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ሀገራዊ የመሻገር ትልሞችን በርብርብና ቅንጅት በማሳካት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር አመራሩ ከምንጊዜውም በላይ የአገልጋይ አመራር ሰብዕና ተላብሶ በውጤታማነት እንዲሠራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጠናው ማጠቃላያ ላይ አቅጣጫ በሰጡበት ወቅት አሳስበዋል፡፡

አመራር አባላቱ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም የሕዝብ ችግሮችን በየደረጃው በመፍታት በተግባር አንድነት የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በስልጠናው በቂ አቅም ማግኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የነገዋን ኢትዮጵያ መሥራት የሚያስችል ግንዛቤ የጨበጡበት ስልጠና መሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡

ስልጠናው ሀገር ቀያሪም ሀብት ፈጣሪም ሰው በመሆኑ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች፣ ከተሞችና የፌዴራል ተቋማት ያለው ከፍተኛ አመራር በተመሳሳይ የፓርቲው ተልዕኮዎች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ለተሻለ ውጤት እንደሚያተጋው አስገንዝበዋል፡፡

መሪነት ራስን መስጠትን፣ ሆደ ሰፊነትንና ዓላማን የማሳካት ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅም አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ከፍተኛ አመራሩ የወሰደው ስልጠናም የመሪነት ቁልፍ መርሆዎችና ባህሪያትን በአግባቡ እንዲገነዘብ ያደረገ ስለሆነ ፈጣንና እመርታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ አቅም ይፈጥራል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.