Fana: At a Speed of Life!

የክፍያ መመሪያን ተግባራዊ ባላደረጉ 4 የግል ትምህርት ቤቶች ለ1 ዓመት የእውቅና ፍቃዳቸው ታገደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)  የኮረና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋትን ተከትሎ መንግስት ያስቀመጠውን የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ መመሪያ ተግባራዊ ባላደረጉኑ አራት የግል ትምህርት ቤቶች ለአንድ አመት የእውቅና ፍቃዳቸው መታገዱን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስተወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ እንደገለጹት፥ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነው የኮረና ቫይረስ መስፋፋትን ተከትሎ የትምህርት ሚኒስቴር ከመጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ መወሰኑ ይታወቃል።

በመሆኑም በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች የገጽ ለገጽ የትምህርት አገልግሎታቸውን እንዲያቋርጡና የአገልግሎት አሰጣጣቸውንም በተለያዩ መንገዶች እንዲያከናውኑ እና የሚያስከፍሉት የአገልግሎት ክፍያም ከ50 እስከ 75 በመቶ እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።

የወጣው መመሪያ ተግባራዊ መሆኑን ለማረጋገጥ በተደረገ ክትትል አብዛኞቹ የግል ትምህርት ቤቶች በመመሪያው መሰረት ተገቢውን ክፍያ በማስከፈል ላይ መሆናቸውን ነገር ግን 21 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ከመመሪያው ውጪ ተገቢ ያልሆነ ክፍያ በመጠየቃቸው በአንድ ሳምንት ውስጥ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ገልጸዋል።

በዚህም 17 ትምህርት ቤቶች ማስተካከያውን ተግባራዊ ማድረጋቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፥ ቀሪዎቹ 4 ትምህርት ቤቶች ግን የክፍያ መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ፍቃደኛ ስላልሆኑ በ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አገልግሎት እንዳይሰጡ ለአንድ ዓመት እውቅና ፍቃዳቸው መታገዱን አስታውቀዋል።

ፍቃዳቸው ከታገደባቸው የግል ትምህርት ቤቶች መካከል በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኙት ለምለም እና ሮማን ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የካ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ስሪ ኤም አካዳሚ እና አራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ገነት መሰረተ ክርስቶስ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ወይዘሮ ሸዊት መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.