Fana: At a Speed of Life!

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎችን የደህንነት መጠበቂያ ቴክኖሎጂ ስራ ላይ አዋለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችል ዲጂታል ቴክኖሎጂ ስራ ላይ ማዋሉን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ፥ ቴክኖሎጂው የተቋሙን ተማሪዎች ደህንነት ለመጠበቅና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን አስተማማኝ ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲው 80 የደህንነት ካሜራዎችና በአምስቱ የመግቢያ በሮች የተማሪዎችን የሚለይ ዲጂታል ቴክኖሎጂን ስራ ላይ ማዋሉን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው በተለይም መታወቂያ፣ ተማሪው የሚማርበት የትምህርት ክፍልና የስንተኛ ዓመት ተማሪ እንደሆነ፣ ማደሪያውና የመመገቢያ (ሚል ካርድ) ቁጥር ለይቶ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ቅጥር ግቢው ውስጥ የሚደረጉ እቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የደህንነት ካሜራዎች ተገጥመው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

በአሁኑ ወቅት የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሁኔታ መኖሩንና ተማሪዎቹም የሁለተኛው መንፈቀ ዓመት ፈተና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ተግባራዊ ያደረገው ቴክኖሎጂ በተማሪዎች መካከል ግጭት የሚፈጥሩ ክፍተቶችን ቀድሞ ለመለየትና ለመከላከል እንዲሁም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ኢዜአ ዘግቧል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.