የብሄራዊ ሎጂስቲክስ ምክር ቤት ተቋቋመ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሄራዊ ሎጂስቲክስ ምክር ቤት በይፋ ተቋቋመ።
የሀገሪቱን የሎጂስቲክስ ችግሮች በዘላቂነት እና ስርአት ባለው መንገድ ለመፍታት፣ በዘርፉ ቁልፍ ሚና ያላቸውን የመንግስት ተቋማት እና የግሉን ዘርፍ ያካተተ ብሄራዊ የሎጂስቲክስ ምክር ቤት ነው የተቋቋመው።
በዛሬው እለትም ምክር ቤቱን ምስረታ በይፋ ለማብሰርና በቀጣይ አሰራሮቹ ላይ ግልጽነት ለመፍጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር የምስረታ ጉባኤ አካሂዷል።
በምስረታ ጉባዔው ላይ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ጨምሮ ሌሎችም የመንግስት እና የግሉን ዘርፍ ተወካዮች ተገኝተዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ወቅት፥ ውስብስብና የማይደፈር የሚመስለው የሎጂስቲክስ ዘርፍ ግልጽ፣ ፈጣንና ዘመናዊ ስርአትን ሊተገብር ይገባል ብለዋል።
የብሄራዊ ሎጂስቲክስ ምክር ቤት በዘርፉ የተቀናጀ አሰራር መኖሩን የሚያረጋግጥ መሆኑ በምስረታ ጉባዔው ላይ ተገልጿል።
እንዲሁም በሎጂስቲክስ ዘርፍ ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን በመለየት የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንደሚያድርግም ነው የተነገረው።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።