Fana: At a Speed of Life!

በክረምት ወቅት የስኳር ፍላጎት አቅርቦትን ለማሟላት 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ለመጠባበቂያ እየተከማቸ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በክረምት ወቅት የስኳር ፍላጎት አቅርቦትን ለማሟላት 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ለመጠባበቂያ እየተከማቸ መሆኑ ተገለጸ።

የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ ከፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ በተያዘው የ2012 ዓ.ም የክረምት ወቅት የስኳር ፋብሪካዎች ወደ ጥገና መግባትን ተከትሎ እስከ 2013 ጥቅምት ወር በሀገሪቱ የስኳር እጥረት እንዳያጋጥም ዝግጀት መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም በሀገር ውስጥ የተመረተ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል በመጋዘን የሚገኝ ሲሆን÷ 2 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ደግሞ ከውጭ ሀገር በመግዛት በቅርቡ ወደ ሃገር ውስጥ ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በክርምት ወራት ፋብሪካዎች ለጥገና ከመዘጋታቸው ጋር ተያይዞ አሁን እየተደረገ ያለው ክምችት በፍላጎትና በአቅርቦት በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ያግዛልም ነው ያሉት።

ከዚያም ባለፈ በዋናነትም በበጋው ወራት  ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ ሲሰራ መወቆየቱን ያነሳሉ።

ለአብነትም በዚህ አመት የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የምርታማነት አቅም በመገንባት ባለፉት 7 ዓመታት አምርቶት የማያውቀውን 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል  ስኳር ማምረት ችሏል ብለዋል።

በሌሎችም ቢሆን ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር አበረታች መሆኑን የገለጹት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፥ የሚቀረውን ለማሟላት በቀጣይ ጊዜያት ትኩረት ሰጥቶ መረባረብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ከማሳደግ በተጨማሪ የክረምቱን መውጣት ተከትሎ በጥቅምት ወር የሚያጋጥም እጥረትን ለማስቀረት ስኳርን በተጠባባቂነት የማከማቸት ስራ ተከናውኗል።

ለዚህም በቀጣይ 2013 ዓ.ም ጥቅምት ወር ድረስ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል በሀገር ወስጥ የተመረተ ከ1 ሚሊየን 100 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት በመጋዝን ተቀምጧል።

ከዚህ በተጨማሪ ለተጠባባቂ ደግሞ ከውጪ 2 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ለማስገባት ውል ስምምነት ተፈጽሟል።

ከዚህ ቀደም ከ3 ሚሊየን በላይ ኩንታል ስኳር በክረምቱ የፋብሪካ ጥገና ምክንያት  ከውጭ በግዥ እንዲገባ ይደረግ እንደነበርም ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።

በዚህም በዘንድሮ የፋብሪካው የማምረት አቅምን ለማሳደግ በመሰራቱ ከውጭ በግዥ የሚቀርበውን  ከ3 ሚሊየን ወደ  2 ሚሊየን ኩንታል እንዲቀንስ ተደረጓል ብለዋል።

የክረምቱ ወራት የጥገና ጊዜ ተከትሎ ከሚፈጠረው የስኳር አቅርቦት እጥረት በተጨማሪ በበጋው ወቅት የስኳር ፍላጎትን ለሟሟላት ይሰራል።

ለዚህም ዘንድሮም ኮርፖሬሽኑ የፋብሪካ፣ የእርሻ ማሽነሪና የመስኖ ፓንፕ የጥገና ስራ ለማከናወን ዝግጅት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መለዋጫዎቹን በፋብሪካውን በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል የሚደረግ ሲሆን÷ አስገዳጅ የሆኑትን ከውጭ መግባት ያለባቸው የጥገና ግብአቶችን የመለየት ስራም መሰራቱን ገልጸዋል።

ለዚህም የውጭ ምንዛሬ የሚያስፈልጋቸው ከውጭ መግባት ያለባቸው የጥገና አስፈላጊ ግብአቶእችን ለመግዛት ኤል.ሲ ተከፍቷል ነው ያሉት

ከዚያም ባለፈ በቀጣይ ዓመት ፋብሪካዎቹ የተሻለ ምርት እንዲያመርቱ የግብዓት አቅርቦትና ተያያዥ ሥራዎችን በተገቢው ጊዜና በተሻለ ጥራት እንዲፈጸም አቅጣጫ  ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል።

በስኳር ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ከሚደረገው ጥረት በተጓዳኝ በፋብሪካዎቹ የኮሮና ቫይረስ በሽታን ለመከላከል ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በተለይም በርካታ ሠራተኞች በሚገኙባቸው የስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የቫይረሱን ሥርጭት በተቀናጀ ሁኔታ ለመከላከል እንዲቻል በአካባቢው ከሚገኙ ማኅበረሰቦች አጋር የልማት ድርጅቶች ጋር በጋራ የመከላከሉ ስራ እየሰሩ ነው።

በታሪክ አዱኛ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.