Fana: At a Speed of Life!

የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለሚያደርገው ተቋማዊ ሪፎርምና ሕግ ማውጣት ስራ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ስራ እየተሰራ ነው- አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚያደርገው ተቋማዊ ሪፎርምና ህግ ማውጣት ስራ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛው የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካደ ነው።

በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እንደተናገሩት÷ ምክር ቤቱ የጥናት ምርምር ውጤቶች ምክር ቤቱ የተሰጠውን የህዝብ ውክልና በሳይንሳዊ መንገድ ለመወጣት እንደሚያግዙ ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ ሣይንሳዊ በሆነ መልኩ ውሳኔዎችን መስጠት እንዲችልና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሥራ እንዲያከናውን የጥናትና ምርምር ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በተለይም ምክር ቤቱ በሕገ-መንግስቱ እና በሌሎች ሕጎች በተሰጡት ተግባራትና ኃላፊነቶች መሠረት የሕግ የማውጣት፣ የክትትልና ቁጥጥር፣ የሕዝብ ውክልናና የፓርላማ ዲፕሎማሲ ስራዎችን በተገቢው መንገድ ለማከናወን ሳይንሳዊ ጥናቶች ሚና አላቸው ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ በየዓመቱ በሚያካሂደው የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስና በሚያደርጋቸው ምርምሮች ላይ ተመስርቶ የተሰጠውን የህዝብ ውክልና ለመወጣት እየሰራ መሆኑን አፈ-ጉባኤው ገልጸዋል።

በኮንፈረንሱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ሚኒስትሮች ፣ የክልል አፈ-ጉባኤዎች፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች፣ የቀድሞው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላትና ሌሎች ባለድርሻዎች መገኘታቸውን ኢዘኤ ዘግቧል።

በየዓመቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት የሚካሄደው የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ በዘንድሮው ዓመትም “ህግ አወጣጥ፣ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የሕዝብ ውክልና“ በሚል የጥናት መስክ ላይ ትኩረት በማድረግ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.