Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ አራት ትዕዛዞችን አወጣ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ማምሻውን አራት ትዕዛዞችን አውጥቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ዛሬ ማምሻውን ተሰብስቦ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተመለከቱ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ገምግሟል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተያዘለት ዓላማ አኳያ አፈጻጸሙ በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም አረጋግጧል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ባወጣው መግለጫ ቁጥር ሦስት፥ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማጠናከርና ዕንቅፋት የሚሆኑትን ችግሮች ለማስወገድ አራት ትእዛዞች አስተላልፏል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ሙሉ ቃል፦

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ መግለጫ ቁጥር ሦስት

ኅዳር 16 ቀን 2014

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ዛሬ ማምሻውን ተሰብስቦ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተመለከቱ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ገምግሟል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተያዘለት ዓላማ አኳያ አፈጻጸሙ በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጧል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማጠናከርና ዕንቅፋት የሚሆኑትን ችግሮች ለማስወገድ የሚከተሉትን አራት ትእዛዞች አስተላልፏል።

1. የመለዮ ለባሾች ዩኒፎርም የራሱ የሆነ የአለባበስ ሕግና ሥርዓት አለው። ከዚህ ሕግና ሥርዓት ውጭ የመለዮ ለባሾችን ዩኒፎርም ለብሶ መገኘት የተልእኮ አፈጻጸሙን እያወከ ይገኛል። በመሆኑም በማንኛውም ሁኔታ፣ ቦታና ጊዜ የመከላከያ ሠራዊትን፤ የፌዴራል ፖሊስን፤ የክልል ልዩ ኃይሎችንና የመደበኛ ፖሊስን ዩኒፎርሞች፣ የጸጥታ አካላት አባል ያልሆነ ማንኛውም ሰው ለብሶ መገኘት ፈጽሞ የተከለከለ ነው። የተቋማቱ አባል ሳይሆንና የታደሰ መታወቂያ ሳይዝ ዩኒፎርሙን ለብሶ በተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ፣ የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ ታዟል።

2 አሁን ያለንበት ሀገር የማዳን የህልውና ዘመቻ በጥብቅ ዲሲፕሊንና በከፍተኛ ጥንቃቄ መፈጸም የሚገባው ነው። ስለሆነም ማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን፣ የጦር ሜዳ ውሎዎችንና ውጤቶችን በተመለከተ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ሥልጣን ከተሰጠው አካል ውጪ፣በየትኛውም የመገናኛ አውታር መስጠትና ማሰራጨት ክልክል ነው። በየግንባሩ የሚገኙ የሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች ከተሰጣቸው ሥምሪትና ተልእኮ ውጭ ማንኛውንም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን፣ የጦር ሜዳ ውሎዎችንና ውጤቶችን የሚመለከቱ መግለጫዎች መስጠት የተከለከለ ነው። የጸጥታ አካላትም ይሄን ተላልለፈው በሚገኙት ላይ አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ ታዟል።

3 በሀገራችን ህልውና ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመቀልበስ መንግሥትና ሕዝብ ተቀናጀተው ወቅታዊና ሕጋዊ ርምጃን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ። ሆኖም ይሄን አጋጣሚ በመጠቀም፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከሚፈቅደው ውጪ የሽግግር መንግሥት ወይም ሌላ ሕገ ወጥ ቅርጽ ያለው መንግሥት እንመሠርታለን ብለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ አካላት ላይ የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ ታዟል ።

4 በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያውያን ግንባር ቀደም አጀንዳ ሀገርን መታደግ መሆኑ ይታወቃል። ማንኛውም የሐሳብና የተግባር እንቅስቃሴ ሁሉ ይሄንን ግንባር ቀደም የኢትዮጵያውያን ዓላማ የማያሰናክል መሆን አለበት። በመሆኑም የሐሳብ ነጻነትን ሰበብ በማድረግ ልዩ ልዩ የሚዲያ አውታሮችን በመጠቀም፣ የሽብር ቡድኑን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በመደገፍ በህልውና ዘመቻው ላይ ዕንቅፋት የሚፈጥሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የአስቸኳይ ጊዜ ዕዝ ያስጠነቅቃል። ይሄንን ማስጠንቀቂያ ተላልፈው ከድርጊታቸው በማይቆጠቡ አካላት ላይ የጸጥታ ኃይሎች ተገቢውን ርምጃ እንዲወስዱ ታዟል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version