አዲስ አበባ ፣ የካቲት 4 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) 33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች መደበኛ ጉባኤና 36ኛው የህብረቱ የሚኒስትሮች ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ በሰላም መጠናቀቁን የፌደራል የፀጥታ ጥምር ግብረ ኃይል ገለፀ።
ግብረ ሃይሉ ጉባኤው ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ በሆነ እንግዳ ተቀባይነትና ጨዋነት ከፀጥታ አስከባሪው ጋር እጅና ጓንት በመሆን ላስመዘገበው ስኬት ምስጋናውን አቅርቧል።
የፀጥታ አካላትም ለፀጥታው መከበር ባከናወነው ተግባር እንዲሁም አጃቢ ሞተረኞችና እግረኛ የትራፊክ ፖሊስ አባላት የትራፊክ ፍሰቱ የተሳለጠ እንዲሆን የበኩላቸውን ሙያዊና የዜግነት ኃላፊነት በመወጣታቸው ሁነቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር መጠናቀቁን አመላክቷል።
አባላቱ ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና ማቅረቡን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና የራይድ ታክሲ አገልግሎት ድርጅት ለፀጥታው ስራ ስኬት በቂ ተሽከርካሪ በማቅረብ ላበረከቱት ጉልህ ድርሻም ከግብረ ሃይሉ ምስጋና ተችሯቸዋል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision