Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሀረሪ ክልል የግጭት መንስዔዎችን የመግታትና ወንጀልን የመከላከል ስራዎች መከናወናቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀረሪ ክልል ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ እንቅስቃሴዎችን የመግታትና ወንጀልን የመከላከል ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት አስታወቀ።

የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት የስራ አፈፃፀም ግምገማ አካሂዷል።

በግምገማው ላይ በክልሉ የሚስተዋሉ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የሀረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከልና የትራፊክ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር አብዲ ኢብራሂም ገልጸዋል።

በተለይም ባለፉት ሁለት ወራት በመሬት ወረራ፣ በጥምቀት በዓል ማክበር ወቅት ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ በርካታ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉንም አስረድተዋል።

ከጥምቀት በዓል አካባበር ጋር ተያይዞ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ተጠርጥረው ከተያዙ 168 ግለሰቦች መካከል 138ቱ ጉዳያቸው ተጣርቶ መለቀቃቸውንም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በወቅቱ ተሰርቀው ከነበሩ 18 የባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች መካከል 17ቱን ማስመለስ መቻሉንም ነው የተናገሩት።

የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል በተሰራ ስራ ግምታቸው 447 ሺህ ብር የሚሆኑ እቃዎችን መያዝ መቻሉንም ጠቁመዋል።

እንዲሁም በሃረር ከተማ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይት ለመከላከል በተሰራ ስራም ከ4 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ መያዝ ተችሏልም ነው ያሉት።

ባለፉት ሁለት ወራት ከህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር ተያይዞ 86 ዜጎች እና 11 ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑንም አብራርተዋል።

ከዚህ ባለፈም ያለ ሰሌዳ ቁጥር አገልግሎት ሲሰጡ የተገኙ 118 ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ተይዘው ህጋዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋልም ብለዋል።

የሀረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ረመዳን ዑመር በበኩላቸው፥ ባለፉት ወራት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ቢሆኑም ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጎልበትና የበለጠ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በየአካባቢው የፀጥታ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችና አዝማሚያዎችን በመለየትና ህዝቡን በማሳተፍ ችግሩን ቀድሞ የማስቀረትና ከምንጩ ማድረቅ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሀረሪ ክልል ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ ናስር ዩያ፥ ከጥምቀት በአል አከባበር ጋር ተያይዞ በስጋት ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ከሀረሪ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version