አዲስ አበባ፣ህዳር 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት አራት ወራት 4 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የሚያወጣ የግብርና ምርት ማገበያየቱን ገለጸ።
ምርት ገበያው በተጠቀሰው ጊዜ 51 ሺህ 640 ሜትሪክ ቶን ቡና፣ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ አረንጓዴ ማሾ፣ የተለያዩ የቦሎቄ ዝርያዎች እና አምስት ቶን የርግብ አተር አገበያይቷል።
የምርቶቹ መጠን 17 ሺህ 690 ቶን ቡና፣ 15 ሺህ 445 ቶን ሰሊጥ፣ 3 ሺህ 24 ቶን ነጭ ቦሎቄ፣ 4 ሺህ 731 ቶን አኩሪ አተር፣ 3 ሺህ 368 ቶን አረንጓዴ ማሾ፣ 1 ሺህ 904 ቶን ዥንጉርጉር ቦሎቄ፣ 215 ቶን ቀይ ቦሎቄና አምስት ቶን የርግብ አተር መሆናቸውን ምርት ገበያው ለኢዜአ የላከው መግለጫ አመላክቷል።
አረንጓዴ ማሾ በዓለም ገበያ ዋጋው እየጨመረ በመምጣቱ ምርት ገበያው የሚገበያይበት ዋጋም በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።
በሐምሌ 2013 ዓ.ም 7 ሺህ 235 ብር የአንድ ኩንታል የአረንጓዴ ማሾ አማካይ የግብይት ዋጋ የነበረ ሲሆን በጥቅምት ወር ወደ 7 ሺህ 841 ብር አድጓል።
ይህ ዋጋ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ መጨመሩን መግለጫው ጠቁሟል።
የገበያው መጨመር አርሶ አደሮችና አቅራቢዎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑም ተገልጿል፤ በመጪው ወር ጥራት ያለው አረንጓዴ ማሾ በከፍተኛ መጠን ለገበያ እንደሚቀርብም ይጠበቃል።
በተመሳሳይ የቀይ ቦሎቄ ግብይት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን ከ50 በመቶ በላይ፤ በዋጋ ደግሞ በእጥፍ ማደጉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ይህ ለውጥ ሊመጣ የቻለው በግብይቱ ላይ ይስተዋል የነበረውን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በመግታትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በመሰራቱ እንዲሁም የደንበኞችን ፍላጎት መሰረተ በማድረግ የአሰራር ማሻሻያ በመደረጉ እንደሆነ አመልክቷል።
ጥቁር አዝሙድ፣ ድንብላል፣ አብሽና ቁንዶ በርበሬ እንዲሁም ጓያ በዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱ የተካተቱ ሲሆን ከተያዘው ምርት ዘመን አንስቶ ግብይት ይካሄድባቸዋል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!