አዲስ አበባ፣ ህዳር 9፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የአፍሪካ አምባሳደሮች፣ ተወካዮች እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከአቶ ደመቀ መኮንን ጋር ተወያዩ።
የልዑካን ቡድኑን በመወከል በኢትዮጵያ የሴኔጋል አምባሳደር ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ሉዑላዊነት እና የግዛት አንድነት በተመለከተ የአፍሪካ አምባሳደሮች የማይናወጥ አቋም እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡
አያይዘውም በህዝብ ከተመረጠው እና ቅቡልነት ካገኘው የኢትዮጵያ መንግስት ጎን እንደሚቆሙኑ እና አጋርነታቸው የጸና መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል የቪዬና ኮንቬንሽን እና የተቀባይ አገር ስምምነትን መነሻ በማድረግ፤ የአስቸካይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ እንዲስተካከሉ የሚፈልጓቸውን ጉዳዮች አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር ለመፍታት አቅሙ እንዳላት እንደማይጠራጠሩና የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ ለሚያደርጉት ጥረት የአፍሪካ አምባሳደሮች ሙሉ ድጋፍ እንደማይለያቸው ገልጸዋል፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ኢትዮጵያ አሁን በገጠማት አስቸጋሪ ሁኔታ፤ በፓን አፍሪካዊነት መርህ፥ አፍሪካውን ወንድሞች እና እህቶች ላሳዩት አጋርነት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ልዩ አክብሮት ያላቸው መሆኑን ገልጸው፤ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አሉ የሚባሉ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት በአገር ደረጃ ሁሉን አቀፍ ውይይት ለመጀመር ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን ያጋጠማቸውን ፈተና በጋራ ለመሻገር በአንድነት እየተረባረቡ መሆኑንም በዝርዝር አብራርተዋል፡፡
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸምና የዲፕሎማቲክ መብቶችን አጠባበቅ አስመልክቶ ለቀረበው ጥያቄ ፤ አዋጁ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡን ጨምሮ የሁሉንም ደህንነት ለማስጠበቅ የወጣ መሆኑና በአፈጻጸም ወቅት የተፈጠሩ ችግሮችን ለማረም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የማጣራት ሥራ ተሰርቶ መፍትሄ እንደሚሰጠው አረጋግጠዋል፡፡
በቀጣይም በዚሁ መልክ ይበልጥ ተቀራርቦ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ለችግሮቹ መፍትሄ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡
አምባሳደሮቹም ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው፤ በቀጣይም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ መድረክ ተዘጋጅቶ ለመገናኘት ፍላጎታቸውን መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን