Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ዞኑ ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት እስካሁን ከ93 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል

 

አዲስ አበባ፣ ህዳር 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎፋ ዞን ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት እስካሁን ድረስ ከ93 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

ዞኑ ከነዋሪዎች ያሰባሰባቸውን 317 ሰንጋዎች፣ 44 በጎች 39 ፍየሎች እንዲሁም 72.25 ኩ/ል ሰንባች ምግብ ነክ ሸቀጦችን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት አስርክቧል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው እንደገለጹት በመጀመሪያው፣በ ሁለተኛው እና በሦስተኛው ዙር በአጠቃላይ ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን የተለያዩ ድጋፎችን በአይነትና በገንዘብ ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

በ4ኛው ዙርም የጎፋ ዞን ነዋሪዎች በከፍተኛ ተነሳሽነትና የሀገር ፍቅር ወኔ ከደጀንነት አስከ ግንባር በነቂስ ለመሳተፍና የኢትዮጵያን አንድነትና ክብር ለመጠበቅና ተገደን የገባንበትን ጦርነት በድል አድራጊነት በአጭር ጊዜ ለመቋጨት ሕዝቡ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መቆሙን በተግባር ማሳየቱን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው አክለው ገልጸዋል።

በአሁኑ 4ኛው ዙር ከአርባ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን በአይነት እና በገንዘብ ለጀግናው መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ መደረጉን ገልጸው፣ እስካሁን ድረስም ዞኑ ከ93 ሚሊዮን ብር በላይ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በዓይነት እና በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉንም አስረድተዋል፡፡

ወደ ፊትም ቀጣይነት ያለው ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ እየተቃጣ ያለውን የሚዲያው ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ እና የውጭ ጣልቃ-ገብነትን ጨምሮ ያሉ ጫናዎችን የጠቀሱት አስተዳዳሪው፣ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን አጠናክረው የትኛውንም ዓይነት ጫና ለመቋቋም እና የክፉዎችን ሴራ ለመቀልበስ ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅማቸውን እያጠናከሩ መጥተዋል ብለዋል።

አሸባሪ ቡድኖች ኢትዮጵያን የጥፋት ቀጠና ለማድረግ የነዙት ፕሮፓጋንዳ በሕዝቡ እና በፀጥታ ኃይሉ የተቀናጀ እርምጃ መክሸፉን የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ማሩፋ መኩሪያ መግለጻቸውን የዞኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያን ጠቅሶ ማቴዎስ ፈለቀ ዘግቧል።

Exit mobile version