አዲስ አበባ፣የካቲት 3፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 1 ነጥብ 5 ሜትር የሚረዝመው ማስታወቂያ ሮቦት በአሜሪካ ታይምስ አደባባይ ስለ ኮሮና ቫይረስ መረጃ ሲሠጥ መዋሉ ተገለጸ፡፡
ወዳጃዊ ፊት የያዘው ይህ ሮቦት ስለ አዲሱ ኮሮና ቫይረስ ምልክቶች እና ህብረተሰቡ ስርጭቱን እንዴት መግታት እንዳለበት በቪድዮ የታገዘ ትምህርት ሲሠጥ ነበር ተብሏል፡፡
በአካባቢው የሚተላለፉ መንገደኞች ቆም ብለው በሮቦቱ ደረት ላይ በተያያዘውና አይፓድ በሚመስል የንክኪ ማያ ገጽ ላይ አጭር ጥያቄ ሲጠይቁና ከማሽኑ ጋር ሲነጋገሩ መዋላቸውም ነው የተጠቆመው፡፡
የማስታወቂያ ሮቦቱ መቀመጫውን ፊላደልፊያ ባደረገውና ለንግድ የሚወሉ ሮቦቶችን በሚያመርት ድርጅት የተዘጋጀ ነው፡፡
የኮሮና ቫይረስ ምልክቶችን ለይቶ ለማወቅ የተለየ ሶፍትዌር መስራታቸውን የኩባንያው የንግድ ሥራ ልማት ሀላፊ ኦሊግ ኪቮርኩስቲቭ ተናግረዋል፡፡
የበሽታውን አስፈሪነት እና ችግሩ ከፍተኛ መሆኑን እንረዳለን ያሉት ሃላፊው ሰዎች ስለኮሮና ቫይረስ ምልክቶችና የመከላከያ መንገድ ጥቂትና ቀላል ነገሮችን ከተረዱ ሁሉም ነገር መልካም ይሆናል ብለዋል፡፡
ሮቦቱ በራሱ ቫይረሱን ለይቶ ማወቅ እንደማይችል የተገለፀ ሲሆን ትኩሳትና የቫይረሱ የተለመዱ የሕመም ምልክቶች በአንድ ሰው ላይ መታየት አለመታየታቸውን በሮቦቱ ማያ ገጾች ላይ አዎ ወይም አይደለም የሚለውን በመንካት ይመርጣሉ ።
በዚህም አይደለም የሚለውን ከመረጡ የማረጋገጫ መልእክት እንደሚቀበሉም ነው የተገለጸው፡፡
ምንጭ፡-ሮይተርስ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision