አዲስ አበባ ፣ የካቲት 2 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ንግድ ድጋፍ የሚውል የ20 ቢሊየን ዶላር የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ።
ስምምነቱን የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ንግድ፥ ከኢስላሚክ ልማት ባንክ፣ ከምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ቢዝነስ ካውንስል እንዲሁም በቆዳ ኢንዱስትሪ ከተሰማሩ 30 ኩባንያዎች ጋር ተፈራርሞታል።
ስምምነቱ የአፍሪካ ስራ ፈጣሪዎችን በተለይም ወጣቶች እና ሴቶችን ለማገዝ እንደሚውል የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ንግድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉዓለም ስዩም ተናግረዋል።
በዚህም በቀጣዮቹ 15 አመታት ውስጥ ለ5 ሚሊየን አነስተኛ እና መካከለኛ ስራ ፈጣሪዎች በዲጅታል ቢዝነስ ድጋፍ በማድረግ ለ125 ሚሊየን ሰዎች ስራ ለመፍጠር ይውላልም ነው ያሉት።
ከዚህ ባለፈም ስምምነቱ በተለይም ወጣቶችን በአፍሪካ ገበያ ላይ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያግዛቸውም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የአፍሪካ ሃገራትን ዘመናዊ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት ለመደገፍና ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነቱን በማገዝ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን አቅም ለማሳደግ ይረዳል ተብሏል።
ስምምነቱ የአፍሪካ ሃገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ኢትዮጵያን በገበያው ላይ ያላትን ተሳትፎ በማሳደግ ተጠቃሚ ያደርጋታልም ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው።
በአወል አበራ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision