አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ .ሲ) ኢትዮጵያ ሰፊ የሰው ኃይልና የገበያ ዕድል የያዘች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሃገር መሆኗን የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የነበራቸውን የ3 ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት በዛሬው እለት አጠናቀው ወደ ሴኔጋል አቅንተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ በኢትዮጵያ የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ እንደነበረ ገልጸዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰው፥ በቆይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ስራዎች ማከናወናቸውን እንደተገነዘቡ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የያዙትን ራዕይ እርሳቸውና ሃገራቸው እንደሚጋሩት በመጥቀስም፥ ሀገራቸው በአቅም ግንባታና በኢኮኖሚ መስክ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያን ምርጫ ቦርድ በመደገፍ ሃገሪቱ የዳበረ ዴሞክራሲ ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዙም ገልጸዋል።
በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከሰለጠነ የሰው ኃይል እስከ ሰፊ የገበያ መዳረሻ የሚዘልቅ ዕድል ይዛለች ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስትዋል።
ይህን ለመረዳት ሩቅ ሳይሄዱ አዲስ አበባን ብቻ መመልከት በቂ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ፥ ለእያንዳንዱ ዜጋ ትክክለኛና እኩል የመስራት እድል ሳይመቻች ስለ ስኬት ማሰብ አይቻልም ብለዋል።
በተለይ ሴቶች የትምህርትና የስራ ዕድል ከተመቻቸላቸው ማህበረሰብን በቀላሉ ከፍ ያደርጋሉም ነው ያሉት።
በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በካቢኔያቸው የጾታ እኩልነትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያን በጉዳዩ መሪ ሃገር እንድትሆን ማስቻላቸውንም ጠቅሰዋል።
ካናዳ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ ዘርፍ በጋራ መስራት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር መፈራረሟንም ይፋ አድርገዋል።
ካናዳ በቀጣዩ ዓመት ከኢትዮጵያ ጋር በመተባባር ከከባቢ አየር ብክለት የጸዳ ቴክኖሎጂ ጉባዔን በአዲስ አበባ እንደምታስተናግድ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision