የሀገር ውስጥ ዜና

ህወሓት የሰብዓዊ ድጋፎችን ለሽብር ድርጊቱ ሲጠቀምበት ነበር – አቶ ደመቀ መኮንን

By Tibebu Kebede

November 05, 2021

 

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪውና ወራሪው ህወሓት ምክንያት በሰሜኑ የአገሪቱ አከባቢ ላሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ በተገቢው መልኩ እንዳይደርስ አድርጓል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

የሚቀርቡ የሰብዓዊ ድጋፎችን ለሽብር ድርጊቱ ተልዕኮ ሲጠቀምበት እንደነበርም ተገልጿል።

አቶ ደመቀ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊ እና የአስቸኳይ ጊዜ የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ከሆኑት ሚስተር ማርቲን ግሪፊትስ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም ም/ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መንግስት በትግራይ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አካላት አስቀድሞ በራሱና ከረጂ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እያቀረበ እንደነበር ገልፀዋል።

ሽብርተኛው ቡድን ከባድ ውድመት እያደረሰ እንኳን ዜጎችን ለመርዳት ከፍተኛ ስራ መሰራቱንም አንስተዋል። መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔን ባሳለፈበት ጊዜም ለዜጎች ከፍተኛ የሆነ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን ጥሎ እንደወጣም አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ የቀጠለው የህወሓት ጠብ አጫሪነት የሰብዓዊ ድጋፉን በሰሜኑ የሀገራችን አከባቢ ላሉ ዜጎች በተገቢው መልኩ እንዳይደርስ አድርጓል ብለዋል። የሚቀርቡ የሰብዓዊ ድጋፎችም ለሽብር ድርጊቱ ተልዕኮ ሲጠቀምበት እንደነበርም ገልጸዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን መንግስት ለሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ከአንዳንድ አካላት እየደረሰበት ያለው ትችት መሬት ላይ ያለውን እውነት ያልተገነዘበ ነው ብለዋል። አለማቀፉ ማህበረሰብም በህወሓት ሽብርተኛ ቡድን ምክንያት ችግር ውስጥ ወድቀው ለሚገኙ በአማራና አፋር ክልሎች ላሉ ዜጎችም እኩል ሊጨነቅ ይገባል ብለዋል።

የአለማቀፉ ማህበረሰብም ሽብርተኛው ቡድን በሀገሪቱ እያደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ ውድመት የሚመጥን ግልፅ ውግዘት ሊያቀርብ እንደሚገባም አቶ ደመቀ ገልጸዋል።

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በሰሜኑ የሀገሪቱ አከባቢ እየተደረገ ያለውን ዝርዝር የሰብዓዊ ድጋፍ በሚመለከትም የብሄራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በማስረጃ የተደገፈ መግለጫ አቅርበዋል።

ሽብርተኛ ቡድኑ እያስፋፋ ባለው ችግር የሰብዓዊ ድጋፎችን መጠቀሚያ እያደረገ መሆኑን አሳውቀዋል። ለዚህም ማሳያው 42,213 ቶን የሚመዝን እህልና ሌሎች ድጋፎችን ጭነው ወደ ትግራይ ከገቡ 1 ሺህ 142 ተሽከርካሪዎች ውስጥ መመለስ የቻሉት 242 ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። ቀሪ ተሽከርካሪዎች ግን ቡድኑ ለሽብር ተግባሩ እየተጠቀመባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ሚስተር ማርቲን ግሪፊትስ በበኩላቸው ለቀረበላቸው ዝርዝር ገለፃ ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል። የእስካሁኑ የሰብዓዊ ድጋፍ ያለ መንግስት ቀና ትብብርና ቁርጠኝነት የማይታሰብ ነበር ብለዋል።

በቀጣይም አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሁሉም ዜጎች እንዲቀርብ ለማድረግ በትብብር መሰራት እንዳለበት መጠየቃቸውን ከሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!