የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባ ፖሊስ ነባሩን የደንብ ልብስ መጠቀም አቆመ

By Tibebu Kebede

November 04, 2021

 

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 25 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጨማሪ አዳዲስ የደንብ ልብሶችን ስራ ላይ ማዋሉን አስታወቀ፡፡

ከዛሬ ጀምሮ አዳዲሶቹ የደንብ አልባሳትን ብቻ መጠቀም እንደሚገባ እና ነባሩን የደንብ ልብስ ሙሉ በሙሉ መቀየሩን ያስታወቀው የአዲስ አበባ ፖሊስ አሮጌውን የደንብ ልብስ ለብሶ የተገኘ አመራርና አባል ላይ ጠንከር ያለ የዲስፕሊን እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጿል፡፡

ህብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት አሮጌው የደንብ ልብስ ሙሉ በሙሉ በአዳዲሶቹ መቀየሩን ተገንዝበው አሮጌውን የደንብ ልብስ የለበሰ የፖሊስ አባል ሲያጋጥማቸው መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩ ጠይቋል።

ፖሊስ ስራ ላይ ካዋላቸው አዳዲስ የደንብ አልባሳት ጋር ወይም ከሌሎች የፀጥታ አካላት የደንብ ልብስ ጋር ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ዩኒፎርም መጠቀም ክልክል መሆኑ በህግ የተደገገ ስለሆነ፤ ከአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ ጋር ተመሳሳይ ዩኒፎርም የሚጠቀሙ አካላት ማስተካከያ እንዲያደርጉ ተቋሙ መልዕክቱን አስተላልፏል።

አዳዲስ ተጨማሪ የደንብ አልባሳቱን ለማስተዋወቅ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፥ በሀገራችን የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ መንግስት የፖሊስ ተቋምን ለማዘመን እየሰራ መሆኑን ተናግረውል።

አዳዲሶቹ የደንብ አልባሳት ደረጃቸውን የጠበቁ በመሆናቸው የተቋማችንን ገፅታ ከመገንባት አኳያ ሚናቸው የጎላ በመሆኑ መላው የአዲስ አበባ ፖሊስ አመራሮችና አባላት የደንብ ልብስ አጠቃቀምን አስመልክቶ በወጣው መመሪያ መሰረት የደንብ ልብሱን በአግባቡ እንዲጠቀሙ አመራሮችም መመሪያውን በአግባቡ እንዲያስፈፅሙ አሳስበዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የፖሊስ ተቋምን ለማዘመን በተያዘው ስትራቴጂካዊ እቅድ የፖሊስ ሰራዊት አርማ እና የደንብ ልብስ እንዲቀየር በተወሰነው መሰረት የአዲስ አበባ ፖሊስ ሰኔ 12 ቀን 2013 ዓ/ም አዲስ የደንብ ልብስ እና የተቋሙን አርማ ሥራ ላይ ማዋሉ ይታወቃል፡፡

ምንጭ:- የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!