አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በወሊድ ወቅት በእናቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሰውን የሞትና ተያያዥ ችግሮችን ለመቀነስ በምታደርገው ጥረት ኖርዌይ ድጋፍ እንደምታደርግ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርና ሶልበርግ ተናገሩ።
በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርና ሶልበርግ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ የካሳንቺስ ጤና ጣቢያን መጎብኘታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሰክረተሪ መረጃ ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርና ሶልበርግ በጉብኝታቸው ወቅት፥ ኢትዮጵያ በምዕተ ዓመቱ የጤና የልማት ግቦች በተለይ የእናቶችና የህፃናትን ሞት በመቀነሱ ረገድ ባለፉት ዓመታት አበረታች ስራዎችን ሰርታለች ብለዋል።
በወሊድ ወቅት በእናቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሰውን የሞት እና ተያያዥ ችግሮችን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረትም የኖርዌይ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ በፕሮጀክት ደረጃ ተግባራዊ ለሚደረጉ “ሴፍ ሊትል ላይፍስ” እና “ካንጋሮ ማዘር ኬር” ለተሰኙ የእናቶችና የህፃናት ጤናን ለመጠበቅ የኖርዌይ መንግሥት የ5 ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።
የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርና ሶልበርግ በከትናንት ጀምሮ በአዲስ አበባ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርና ሶልበርግ በትናንትናው እለትም ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ከዚህ ባለፈ በኢትዮጵያ ቆይታቸው በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ከሚገኙ የሀገራት መሪዎች እንደሚወያዩ ተጠቁሟል።
እንዲሁም ከህብረቱ ጎን ለጎን በሚካሄዱ ውይይቶች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ይሳተፋሉ ተብሏል።