Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጠቅላይ ፍርድቤት መልካም አፈጻጸም ላስመዘገቡና አርዓያ ለሆኑ ሠራተኞቹ ዕውቅና ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መልካም አፈጻጸም ላስመዘገቡና እና አርዓያ ለሆኑ ዳኞች፣ ረዳት ዳኖችና አስተዳደር ሰራተኞች ዕውቅና ሰጠ፡፡
ፍርድ ቤቱ እውቅና የሰጣቸው እና ያመሰገናቸው ዳኞች፣ ረዳት ዳኞችና ሬጂስትራሮች÷ የሙያ ብቃትና ስነምግባር፤ የመዝገብ አፈጻጸም፣ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት እና የተገልጋይ አያያዝን እንደመስፈርት ተጠቅሞ የመረጣቸው ናቸው ተብሏል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ በቅርቡ ሁለት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች በወንጀል ተጠርጥረው በህግ ጥላ ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
በአንድ በኩል በፍርድ ቤት ውስጥ እንዲህ ዓይነት የሙያና የስነምግባር ጉድለት መኖሩ ያሳዘናች መሆኑን÷ በሌላ በኩል ደግሞ የስነምግባር ጉድለት ያለባቸውን ዳኞች ከፍርድ ቤቱ የማጥራት ስራ አስፈላጊነትን ለአመራሩ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት ፍርድ ቤቶች በዳኝነት ነጻነትና ገለልተኝነት ላይ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀሳቸውን አስታውሰው÷ ከዚህ በኃላ የዳኝነት ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ዳኞች ህዝብና መንግስት የሰጧቸውን የመዳኘት ኃላፊነት በነጻነት፣ በገለልተኝት እና በታማኝነት ሊወጡ ይገባል ያሉት ፕሬዝደንቷ÷ ርትዕ ዳኝነት ፈልገው ፍርድ ቤት የሚመጡ ተገልጋዮችን ሲያስተናግዱ ዳኞች ትዕግስት እና ጉዳዮችን የሚመረምሩበት ክፍት አእምሮ ሊኖራቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡
በአክብሮትና ቃልን ባከበረ ሁኔታ ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው እንዲሁም ራሳቸውን በባለጉዳይ ቦታ አስቀምጠው ማሰብ እንደሚያስፈልጋቸው ማሳሰባቸውን ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!!
Exit mobile version